የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

በፓርኩ የሚቀነባበሩ ምርቶች ጥራታቸውና ደህንነታቸው የተረጋገጠና ከብክነት የጸዳ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው

Apr 3, 2025

IDOPRESS

ሀዋሳ ፤መጋቢት 24/2017 (ኢዜአ) :- በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚቀነባበሩ ምርቶች ጥራታቸውና ደህንነታቸው የተረጋገጠና ከብክነት የጸዳ እንዲሆኑ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

በፓርኩ ለሚሰሩ ፋብሪካዎችና ባለድርሻ አካላት በምግብ ደህንነት፣ ቁጥጥርና ደረጃ አሰጣጥ ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡


የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሃይሉ የተራ ለኢዜአ እንደገለጹት በፓርኩ የሚቀነባበሩ ምርቶች ጥራትና ደህንታቸው የተረጋገጠና ተገቢው ቁጥጥር የተደረገላቸው እንዲሆኑ እየተሰራ ነው፡፡

በዋናነትም በፓርኩ የሚሰሩ ባለሃብቶችን ግንዛቤ ለማሳደግ ከኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅተን እየሰራን ነው" ብለዋል፡፡

በዚህም ወደ ፋብሪካው የሚገቡ ጥሬ ግብዓቶች ከአርሶአደሩና ማህበራት ከመሰብሰብ እሴት ጨምሮ ለገበያ እስኪቀርብ ጥራቱን የጠበቀ፣ደህንነቱ የተረጋጋጠና ከብክነት የጸዳ እንዲሆን ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው ቀጣይነት ያለው መሆኑን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው በገበያ ተወዳደሪ መሆን የሚችሉ አምራቶችን ለመፍጠርና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

በፓርኩ እሴት የተጨመረባቸውን የግብርና ምርቶችን የሚያቀነባብሩ ባለሃብቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው በዘንድሮ አመትም አራት ፋብሪካዎች ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

"በፋብሪካው የሚሰሩ ባለሙያዎች ግንዛቤ በማሳደግ ጥራት ያለውን ምርት ለማምረት ኮርፖሬሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ሃዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ንማኔ በበኩላቸው ወደ ፓርኩ ለሚገቡ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከምግብ ደህንነት ጋር የተያያዙ መስፈርቶች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለህብረተሰቡ እንዲቀርብ የማድረግ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸው "ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል፡፡

በስልጠናው ያገኙት እውቀት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል አቅም የሚፈጥር መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጎልደን ኦርጋንኪ አቦካዶ ማቀነባባሪያ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ተፈሪ አሜና ናቸው፡፡

የዶሊ ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ፕሮዳክሽን ማናጀር ሜሮን አየለ በበኩላቸው በፋብሪካው የሚቀነባበሩ የህጻናት ምግቦች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ በስልጠናው ተገቢውን እውቀት ማግኘቷን ገልደዋል፡፡

በስልጠናው በፋብሪካው ምርቶችን የሚያቀነባብሩ ባለሃብቶችን ጨምሮ ባለሙያዎችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣንና በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት አማካይነት የተለያዩ ሰነዶች ቀርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.