የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

ወጣቶቹ የኮደርስ ስልጠና በዘርፉ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን እውቀት እያገኙበት መሆኑን ገለጹ

Apr 7, 2025

IDOPRESS

ሐመር-ዲመካ፤መጋቢት 27/2017(ኢዜአ፦ በኮደርስ ስልጠና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን ዕውቀት እየቀሰሙ እንደሚገኙ በደቡብ ኦሞ ዞን በኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ላይ የተሳተፉ ወጣቶች ገለፁ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢንሺዬቲቭ በሀገሪቱ በዲጂታል ክህሎት የታገዘ ማህበረሰብን ለመፍጠር የሚያግዝ የኢትዮ -ኮደርስ ስልጠና በሁሉም አካባቢዎች እየተሰጠ ነው።

በስልጠናው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የደቡብ ኦሞ ዞን ወጣቶችም በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን ዕውቀት እየቀሰሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል ።

በዞኑ የዲመካ ከተማ ነዋሪ ወጣት በረከት ጀምጀም የዳታ ሳይንስ ስልጠና እየወሰደ የሚገኝ ሲሆን በስልጠናው እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ዕውቀቶችን መቅሰሙን ጠቅሶ፥ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆንበትን ዕድል ማግኘቱንም ተናግሯል ።

ከስልጠናው ስለ ዲጂታል ማርኬቲንግ እና ስለ ኦንላይን ቢዝነስ ጠቃሚ ዕውቀቶችን መቅሰሟን የገለፀችው ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ ወጣት አትጠገብ መሰረት ናት።


በኦንላይን ቢዝነስ ከአገር ውስጥ ባለፈ ከውጭ ሀገራት ኩባንያዎች ጋር በበይነ መረብ አማካኝነት ካለችበት ቦታ በመሆን መስራት የምትችልበትን እና በትርፍ ሰአቷ ተጨማሪ ገቢ የምታገኝበት ዕድል መፈጠሩን ተናግራለች።

በዞኑ የዳሰነች ወረዳ ነዋሪ ወጣት ግርማ አያሌው በበኩሉ፥ ከስልጠናው ጊዜን፣ ጉልበትንና ገንዘብን ቆጣቢ የሆኑ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም ስራውን በፍጥነት እና በብቃት ማከናወን የሚችልበትን ዕውቀት እንዳገኘ ገልጿል ።


የደቡብ ኦሞ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሪት ብሩክታዊት አኮ በበኩላቸው፥ በዞኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረውን የኢትዮ -ኮደርስ ኢንሺዬቲቭ ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

በዞኑ በቀጣይ ሶስት ዓመታት ከ13 ሺህ ለሚልቁ ወጣቶች የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ለመስጠት መታቀዱን ጠቅሰው፥ በዚህ ዓመትም ከ 1 ሺህ 600 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ስልጠናው በበይነ መረብ አማካኝነት እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።


የጂንካ ዩኒቨርስቲም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው የኢትዮ-ኮደርስ አገራዊ ኢንሺዬቲቭ ውጤታማ እንዲሆን በአካባቢው ላሉ ዞኖች የክህሎትና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ተወካይ መምህር ዳዊት ደንዳኖ ተናግረዋል።


የዩኒቨርስቲው መምህራን እና ተማሪዎች በስልጠናው ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቅሰው፥ የአካባቢው ማህበረሰብም የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን በማበረታታት፣ የክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠትና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ235 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ከክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.