የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

ሚኒስቴሩ አማራጭ የኃይል አቅርቦትን በመጠቀም ከኤሌክትሪክ መስመር ለራቁ አካባቢዎች ኃይል ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው

Apr 8, 2025

IDOPRESS

ሚዛን አማን፤ መጋቢት 29/2017(ኢዜአ)፦ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አማራጭ የኃይል አቅርቦትን በመጠቀም ከኤሌክትሪክ መስመር ለራቁ አካባቢዎች ኃይል ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን በ60 ሚሊዮን ብር የተገነባ የጸሐይ ኃይል ፕሮጀክት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።


የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ(ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ያልሆኑ ዜጎችን በአማራጭ የኃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በተለይ ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው ለሚገኙ ዜጎች የጸሐይ ኃይል አማራጭን በመጠቀም የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


ለአብነትም በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ 5ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የይርኒ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትም የዚሁ አካል መሆኑን አንስተዋል።

መንግሥት የኃይል አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ በሰጠው ትኩረት ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት ውስጥ ከ2 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ታዬ ናቸው።

በሌላ በኩል በገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ለ1ሺህ 380 የገጠር ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ማዳረስ መቻሉንም አክለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረማርያም ሰጠኝ በክልሉ ከ200 እስከ 850 ኪሎ ዋት የሚያመነጩ 8 የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ይህም ከዋና መስመር ርቀው ለሚገኙ ዜጎች የኃይል አማራጭን ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል።

የምዕራብ አሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ወንድሙ ቦንባ የጸሐይ ኃይል አማራጭ አገልግሎቱ ለዞኑ ሁለተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱ የዘመናት የሕዝቦችን የኃይል አቅርቦት ጥያቄን የፈታ መሆኑንም አንስተዋል።

ዛሬ በዞኑ መኤኒት ሻሻ ወረዳ የተመረቀው የጸሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 100 ኪሎ ዋት ኃይል የሚያመነጭ ነው።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.