የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ምርታማነትን እያሳደገ ነው- ሚኒስትር መላኩ አለበል

Apr 9, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፣መጋቢት 30/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ምርታማነትን በማሳደግ በተኪ ምርት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።


ሚኒስትሩ ፕራይም ቴክ የተሰኘ የሲኤንሲ ማሽን ማምረቻ እና የብረት፣ የፕላስቲክና የእንጨት ውጤቶች ላይ የሚሰሩ የተለያዩ ቅርጻቅርጾችን በቴክኖሎጂ በተደገፈ አሰራር የሚያመርት ድርጅትን ጎብኝተዋል።


ጉብኝታቸውን ተከትሎ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ፥ መንግስት የሀገር ውስጥ አምራቾችን የሚያበረታቱ አሰራሮችን እየተገበረ ነው ብለዋል።


በተለይም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራቾች የመስሪያ ቦታ፣ የፋይናንስና መሰል ድጋፎች እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል።


ንቅናቄውን ተከትሎ ወደ ሥራ የገቡ ኢንዱስትሪዎች ያሉበትን ደረጃና የፈጠሩትን የገበያ ትስስር በሚመለከት በየወቅቱ ምልከታ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።


ፕራይም ቴክ የሲ.ኤን.ሲ ማሽን ማምረቻ ድርጅት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጥሩ የገበያ ትስስር ከፈጠሩ አምራቾች መካከል ተጠቃሽ ነው ብለዋል።


ድርጅቱ የኢትዮጵያውያንን የፈጠራ አቅም፣ ችሎታና የወደፊት ተስፋን አጉልቶ እንደሚያሳይም ገልጸዋል።


ከዚህ ቀደም ማሽኖችን ለማምረት በብረት፣ በፕላስቲክና በእንጨት ውጤቶች ላይ የሚሰሩ የተለያዩ ቅርጻቅርጽና ዲዛይኖችን ለማውጣት ወደ ውጪ ሀገራት በመላክ ወይም በከፍተኛ የሰው ጉልበት ይሰራ እንደነበር አንስተዋል።


ፕራይም ቴክ ሲ.ኤን.ሲ ማሽኖችን በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ ማምረት መጀመሩ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍና ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ተወዳዳሪነትና ተፈላጊነት ከፍ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።


ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከአገር ውስጥ አልፎ የውጪ ገበያ ትስስር እየፈጠረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።


ይህም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ምርታማነትን በማሳደግ በተኪ ምርት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት።


የፕራይም ቴክ ሲ.ኤን.ሲ ማሽን ማምረቻ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሁንዴ ኤባ፥ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በብዛትና በጥራት ለማምረት መንግስት የሚያደርገው ድጋፍ የሚበረታታ ነው ብለዋል።


በድርጅቱ ዓለም አቀፍ ጥራታቸውን የጠበቁ የሲኤንሲ ማሽኖችን በቴክኖሎጂ በተደገፈ አሰራር እያመረተ መሆኑን ተናግረዋል።


ማሽኖቹ የብረት፣ የፕላስቲክና የእንጨት ውጤቶችን ለተፈለገው ዓላማ ቅርጽ አስይዞ ማምረት የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።


በአሁኑ ወቅትም ምርቶቹን ለተለያዩ የግንባታና ኮንስትራክሽን ዘርፎች በግብዓትነት እያቀረበ እንደሚገኝ አብራርተዋል።


በአንድ ወር ውስጥ ከ10 በላይ ማሽኖችን የማምረት አቅም ያለው ድርጅቱ፥ ለሠላሳ ሰዎች ቋሚ የስራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።


የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ድርጅቱ ምርቱን ከሀገር ውስጥ ገበያ ባሻገር ለኡጋንዳ ማቅረብ የሚችልበትን እድል እንደፈጠረለት ገልጸው፥ በቅርቡም ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለማቅረብ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.