የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ፖለቲካ እና ደህንነት

የውሃ ሀብትን በዘላቂነት ማስተዳደርና መጠቀም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው-የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

Apr 9, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፣መጋቢት 30/2017(ኢዜአ)፦የውሃ ሀብትን በዘላቂነት ማስተዳደርና መጠቀም የሚያስችል ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።


የተቀናጀ የተፋሰስ አስተዳደር ፕሮጀክት (ብራይት ፕሮጀክት) በአባይ፣ አዋሽ እና ተከዜ ተፋሰሶች ላይ በይፋ ተጀምሯል።


የተቀናጀ የተፋሰስ አስተዳደር ፕሮጀክቱ የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በጋራ የሚተገብሩት የ5 አመት ፕሮጀክት ነው።


የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፥መንግስት በሀገሪቱ በሚገኙ የውሃ ሀብቶችን ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ጥቅም ላይ ለማዋል የተቀናጀ የውሀ አስተዳደር መቀረጹን ተናግረዋል፡፡


ይህንንም ተከትሎ የውሀ ሀብቱን በዘላቂነት ለመጠቀምና ለማስተዳደር የሚያስችል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።


ዛሬ በአባይ፣አዋሽ እና ተከዜ ተፋሰሶች ይፋ የተደረገው የተቀናጀ የተፋሰስ ፕሮጀክት እና ሌሎች ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኙ ለአብነት አንስተዋል፡፡


እነዚህ እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶች የውሃ ሃብትን ከመጠቀም አንጻር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።


የዛሬውን ፕሮጀክት ጨምሮ ሌሎች የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ በተቀናጀ አግባብ መምራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡


ህብረተሰቡን ማሳተፍ እንደሚገባም ጠቁመው ለዚህም መዋቅር መዘርጋቱን ተናግረል፡፡


የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ጌቴ ዘለቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በፕሮጀክቱ በውሃ ሃብት ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት የሚከናወኑበት መሆኑን አመልክተዋል።


በዚህም ለውሃ እጥረት፣ ብክለትን ለመከላከልና ለስነ-ምህዳር መጎሳቆል መንሴኤዎች የሆኑ ጉዳዮችን መከላከል የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚሰሩ አስገንዝበዋል።


ፕሮጀክቱ የተፋሰሱን ነዋሪዎች ኑሮ ማሻሻልና ለአየር ንብረት ለውጥ ስጋቶች የማይበገር አካባቢ ማረጋገጥን ያለመ መሆኑም ገልፀዋል፡፡


የአማራ ክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን ሽመልስ እና በኦሮሚያ የውሀ ኢነርጂ ቢሮ የውሃ ሃብት ዳይሬክተር ተሻለ በቃና በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ የውሃ ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም እና ለማስተዳደር ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።


ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲሆን በቀጣይ የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር ውጤታማ ተግባራት ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡


በኔዘርላንድስ ኤምባሲ እና በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበረው ፕሮጀክት በውሃና መሬት ሀብት ማዕከል በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባሉ የዓባይ፣ አዋሽ፣ ተከዜ፣ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች እና ኦሞ ግቤ የተፋሰስ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የሚተገበር መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.