የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በጉጂ ዞን በበልግ አዝመራ ከ160 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል

Apr 11, 2025

IDOPRESS

አዶላ፤ ሚያዝያ 2/2017(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በበልግ አዝመራ ከ160 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በዞኑ በየአመቱ ከመጋቢት 15 እስከ ሚያዝያ መጨረሻ የዝናብና የበልግ አዝመራ የዘር ወቅት ሲሆን በጉጂ ዞን ከሚገኙ 13 ወረዳዎች መካከል አዶላ ሬዴ፣ ዋደራ፣ ሰባቦሩ፣ ግርጃ፣ አጋ ወዩና ሻኪሶ በልግ አብቃይ እንደሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ሀላፊ አቶ ቂልጣ ጂማ፤ ዘንድሮ በዞኑ የበልግ አዝመራ 254 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡


በዞኑ ስድስት ወረዳዎች እስካሁን በተሰራው ስራ 162 ሺህ 560 ሄክታር መሬት በዋናነት በስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ገብስና ቦለቄ ዘር መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡

በተያዘው ዓመት የበልግ አዝመራ ምርታማነትን የሚጨምሩ አዳዲስ የግብርና መካናይዜሽን አሰራሮች መመቻቸታቸውን ጠቅሰው በዚህም የኩታገጠም አስተራረስ ዘዴ፤ የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦት ዋናዎቹ እንደሆኑም አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም በዞኑ እስካሁን 95 ሺህ 600 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና 37 ሺህ 334 ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መቅረቡን አስታውሰዋል፡፡

በበልግ አዝመራ ከሚለማው መሬትም 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡


በዞኑ አዶላ ሬዴ ወረዳ የደራርቱ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አቶ ዳዴ ደርሶ፤ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን በበልግ አዝመራ ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡

ለበልግ አዝመራ ያዘጋጁትን አንድ ሄክታር መሬታቸውን በዘር መሸፈናቸውን ገልጸዋል፡፡

ለዘንድሮ በልግ አዝመራ ካዘጋጁት መሬት ከ30 ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርት እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል፡፡


የዚሁ ወረዳና ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ወገኔ ክፍሌ ከሌሎች ስድስት አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር ስድስት ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም አስተራረስ በዘር መሸፈናቸውን ገልጿል፡፡

''ከሰብሉም እስከ 180 ኩንታል የበቆሎ ምርት ለማግኘት አቅደን እየሰራን ነው'' ያለው ወጣቱ መንግስት የግብርና አሰራሮች በማመቻቸት ድጋፍና ክትትል እያደረገላቸው መሆኑን አሳውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.