የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በከተማዋ ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ ደንቦችና መመሪያዎችን ከወቅቱ ጋር ማጣጣም ይገባል

Apr 15, 2025

IDOPRESS

ደብረ ማርቆስ፤ሚያዚያ 6/2017 (ኢዜአ)፦በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ሁለንተናዊ ሆነው የህዝቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ የወጡ ደንቦችና መመሪያዎችን ከወቅቱ ጋር ማጣጣም እንደሚገባ የከተማዋ አስተዳደር ምክር ቤት አስገነዘበ።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ባካሄደው የ2017 በጀት ዓመት 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የተለያዩ ደንቦችን አጽድቋል።


የከተማ አስተዳደሩ ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ መርከብ የሻነህ በጉባኤው ላይ እንደገለጹት የከተማዋን ልማትና እድገት ለማፋጠን ደንቦችና መመሪያዎችን ከወቅቱ ጋር የተጣጣሙ ማድረግ ይገባል።

የመንቆረር ኮንስትራክሽን ድርጅት የከተማ አስተዳደሩ ያቋቋመው የልማት ድርጅት መሆኑን አንስተው ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው ጉባኤም የድርጅቱን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ማጽደቁን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች ደህንነት አጠባበቅ መመሪያን አፅድቋል ብለዋል።

የመንቆረር ኮንስትራክሽን ድርጅት ደንብን የማሻሻል ዓላማም ድርጅቱን በሰው ሃይል፣በማሽነሪና በአሰራር በማዘመን የኮንስትራክሽን ዘርፉን ብቁና ተወዳዳሪ ለማድረግ መሆኑን አመልክተዋል።

በደንቡ ላይም በኮሪደር ልማቱ ላይ ግብይት የሚፈጽም፣ቆሻሻ የሚጥል፣ ዝቃጭ የመኪና ዘይት የሚደፋና ሌሎች ጥፋቶችን የሚፈጽሙ አካላት ከሶስት እስከ አምስት ሺህ ብር ቅጣት እንደሚተላለፍባቸው በደንቡ መደንገጉን ገልጸዋል።

ይህም የከተማዋን ገጽታ በመገንባት፣ጽዱና ውብ በማድረግ ቱሪዝምንና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ በበኩላቸው፥ ደንቦቹ የከተማዋን እድገት ለማፋጠን አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ድርጅቱ ከአሁን በፊት ይሰራው ከነበረው የመንገድና የህንጻ ግንባታና የነዳጅ ማቅረብ ስራ በተጨማሪ በውሃ ተቋማት ግንባታ እንዲሰማራ የሚፈቅድ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም በተለያዩ ከተሞች ቅርንጫፍ በመክፈት ፈጣንና ቀልጣፋ አሰራርን በመዘርጋት ተወዳዳሪነቱን እንዲያሳድግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አስማማው አጥናፉ እንዳሉት የተሻሻለው ደንብ ድርጅቱን በክልሉና በአገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

ምክር ቤቱ ደንቦቹ በአግባቡ ተተግብረው በከተማዋ እድገት ላይ የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ በአስፈጻሚ አካላት ላይ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሌላዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ሙሉወርቅ አበበ በበኩላቸው፥ የመመሪያው መሻሻል ድርጅቱ ያሉበትን ክፍተቶች በመሙላትና አዳዲስ አሰራሮችን በመጨመር በቀጣይ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችለው ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.