አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 6/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት አሁን ላይ በ63 ከተሞች እየተከናወነ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነትና አመራር ሰጪነት በርካታ ከተሞች ጽዱና ምቹ የመኖሪያና የማምረቻ ማዕከል እየሆኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለሁሉም ዘርፎች እየሰጡ ባሉት የአመራር ድጋፍና ክትትል እንዲሁም በሕዝቡ ተሳትፎ ከዕቅድ በላይ አፈጻጸም መኖሩንም ነው የገለጹት።
ይህ ዘመን የከተሞች የህዳሴ ዘመን ነው ያሉት ሚኒስትሯ የኮሪደር ልማቱ የበርካታ ከተሞችን መሠረተ ልማት በማሻሻል አካታች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ የተገኘውን ተሞክሮውን በማስፋት በአሁኑ ወቅት በ63 ከተሞች የኮሪደር ልማቱ እየተተገበረ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
በዚህም በብዙ ከተሞች የተጎሳቆሉና በአረንቋ ውስጥ የቆዩ ሰፈሮች ሙሉ ለሙሉ ተቀይረው ዘመናዊ፣ ውብና ምቹ የመኖሪያ፣ የሥራና የመዝናኛ ማዕከል እየሆኑ ነው ብለዋል።
በኮሪደር ልማቱ የተሽከርካሪ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ፣ የመብራትና ሌሎችም የአገልግሎት መሰረተ ልማቶች በስፋት ተገንብተው ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
ይህም መንግሥት በሁሉም አካባቢ ፍትሐዊ ልማትን ተደራሽ ለማድረግ የጀመረውን ጉዞ የሚያሳካ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም ከለውጡ በፊት 74 በመቶ የከተሞች ክፍል ደረጃውን ያልጠበቀና የተጎሳቆለ እንደነበር በማውሳት ከለውጡ ወዲህ በተከናወኑ የኮሪደር ልማትና ሌሎች ሥራዎች መሻሻል መጥቷል ነው ያሉት።
የኮሪደር ልማቱ ከተሞችን የፈጠራ፣ የምርምር፣ የአዳዲስ ሀሳቦች መፍለቂያ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ ከሸማችነት ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ ዕድል መፍጠሩንም አንስተዋል።
የከተማ የአረንጓዴ ሽፋንም 5 በመቶ ከነበረበት ወደ 22 በመቶ ከፍ ማለቱን አስረድተዋል።
ሚኒስትሯ አያይዘው እንደገለጹት ከኮሪደር ልማት ባሻገር በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተፋጠኑ ነው ብለዋል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025