የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነትን በቅርቡ መተግበር ትጀምራለች-ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

May 6, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 27/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነትን በቅርቡ መተግበር ትጀምራለች ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።


የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሳምንትን አስመልክቶ ሁለተኛው የኮሜሳ ተቋማዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በፎረሙ መክፈቻ እንደገለጹት፥ ከአገራዊ ለውጥ በኋላ ቀጣናዊ የንግድ ትስስርን ለማሳደግና የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገች ያለው ጥረት ወደ ውጤት እየመጣ ነው።


ኢትዮጵያ የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ አባል ከሆነች ከሃያ ዓመታት በላይ ቢቆጠሩም የገበያው ተጠቃሚ እንዳልነበረችም ነው ያስታወሱት።


የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሐሙስ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት የዕቃዎች ቀረጥ ምጣኔ ቅነሳን ለማስፈፀም በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቷል።


ስምምነቱ በአባል አገሮች መካከል ንግድ እንዲስፋፋ፣የገበያ ትስስሩ እንዲጠናከር፣ የእሴት ሰንሰለቱ እንዲጎለብትና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እንዲበረታታ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።


በአባል አገሮች መካከል የሚደረጉ ግብይቶች በታሪፍ ምክንያት ሳይደናቀፉ የእቃዎች ፍሰት የተሳለጠ እንዲሆን ከአባል አገሮች በሚመጡ እቃዎች ላይ የጉምሩክ ታሪፍ ምጣኔ ለይቶ መወሰን አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።


ምክር ቤቱ ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተፈፃሚ እንዲሆን በሙሉ ድምጽ መወሰኑን ተከትሎ ከጥቂት ቀናት በኋላ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነትን መተግበር ትጀምራለች ብለዋል።


እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ኢትዮጵያ ለአህጉሪቷ የንግድ ውህደት እያደረገች ባለው አስተዋጽኦ የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሳምንትን እንድታዘጋጅ ተመርጣለች።


አገሪቷ በግብርና፣በማዕድንና በቱሪዝም ዘርፉ እምቅ አቅሞቿን በመጠቀም በገበያው ያላትን ድርሻ ለማስፋት የሚያስችላት መሆኑንም አመልክተዋል።


ሃያ አንዱ የኮሜሳ አባል አገሮች በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲረዱ ጉብኝትን ጨምሮ የተለያዩ የፓናል ውይይቶች መዘጋጀታቸውን ነው ያመለከቱት።


ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገው ድርድርና ቀጣናዊ የንግድ ትስስሮችን ለማሳለጥ እያደረገች ያለው ጥረት ለሌሎች አገሮች ተሞክሮ መሆኑንም አመልክተዋል።


የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ዋና ፀኃፊ ቺሌስ ካፕዌ፤ ለአየር ንብረት ተፅዕኖ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የፈጠራ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ለንግድ ሥራ ፈጣሪዎች ተገቢው ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡


የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ የሴቶች ቢዝነስ ፌዴሬሽን ሰብሳቢ ማውረን ሱምቤ፤ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ያላቸውን አቅም አውጥተው እንዲጠቀሙ ዕድሉን ማመቻቸት ይገባል ብለዋል።


ኮሜሳ ሴቶችን በቴክኖሎጂ በማብቃትና ተጠቃሚ በማድረግ የገበያ እድል እንዲመቻችላቸው እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡


የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሳምንት "የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የግብርና፣ ማዕድን እና ቱሪዝም የእሴት ሰንሰለቶችን በማጎልበት ክልላዊ ውህደትን ማፋጠን" በሚል መሪ ሀሳብ በተያዩ ሁነቶች ይከበራል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.