የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የኢትዮጵያን ነፃነት ለማስጠበቅ የተከፈለውን መስዋዕትነት በልማት ስኬት መድገም ይገባል-አባት አርበኞች

May 6, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 27/2017 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያን ነፃነት ለማስጠበቅ የተከፈለውን መስዋዕትነት ትውልዱ በልማት ስኬት መድገም እንደሚገባው አባት አርበኞች አስገነዘቡ።


አባት አርበኞች ዛሬ ሶስተኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ጎብኝተዋል።


በጉብኝቱ ላይ የተገኙት አርበኛ አስማማው መከተ፥ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ትውልዱ የሚያኮራ ታሪክ እየሰራ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል።


በኤክስፖው በተለይም የስራ እድል መፍጠር የሚችሉና ሀገሪቱን ሊያሻግሩ የሚችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በተጨባጭ ተመልክተናል ነው ያሉት።


ሻምበል አበበ አለሙ በበኩላቸው፥በተለያዩ አውደ ውጊያዎች በመሳተፍ አኩሪ ገድል ማስመዝገባቸውን አስታውሰው፤ የአሁኑ ትውልድ በልማት የራሱን የጀግንነት ታሪክ እየፃፈ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።


አባት አርበኞቹ የኢትዮጵያን ነፃነት ለማስጠበቅ የተከፈለውን መስዋዕትነት በልማት ስኬት መድገም እንደሚገባ ገልጸዋል።


የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላችው፥ ጀግኖች አርበኞች የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር የከፈሉት መስዋዕትነት ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።


የአሁኑ ትውልድ ኢትዮጵያን ከድሕነት ሊያወጡ በሚችሉ የልማት ተግባራት ላይ በመሳተፍ የሀገሩን ብልጽግና ማረጋገጥ ይጠበቅበታል ብለዋል።


አባት አርበኞች በዘመናቸው የራሳቸውን የጀግንነት ገድል እንደፈፀሙ ሁሉ ቀጣዩ ትውልድ የራሱ የሆነና የሚኮራበትን ታሪክ መስራት አለበት ብለዋል።


በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እውን ማድረግ ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፥ የአሁኑ ትውልድ አርበኝነት ከምርታማነት ጋር መያያዝ እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡


በተለይም ኋላቀርነትን በማስወገድ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት በማምረት ድሕነትን መዋጋት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የተዘጋጀውን ሦስተኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በይፋ መክፈታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.