የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የፓኪስታን-አፍሪካ የንግድ ልማት ጉባኤና አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ይካሄዳል-አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ሚያን

May 8, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 29/2017(ኢዜአ)፦5ኛው የፓኪስታን-አፍሪካ የንግድ ልማት ጉባኤና አውደ ርዕይ ከግንቦት 7 እስከ 9/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ሚያን ገለጹ።

5ኛው የፓኪስታን-አፍሪካ የንግድ ልማት ጉባኤና አውደ ርዕይ አስመልክቶ አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ፤ የፓኪስታን ንግድና ኢንቨስትመንት ሚኒስትር ባሲጥ ሳሊም ሻህ በተገኙበት መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደሩ በሰጡት መግለጫ በፓኪስታን-አፍሪካ የንግድ ልማት ጉባኤና አውደ ርዕይ ላይ ከ100 በላይ የፓኪስታን አምራችና ላኪ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎታቸውን ያቀርባሉ ብለዋል።

በዚህም ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የንግድ ትስስርን የሚያጠናክሩ የሕክምና መድኃኒት ምርትና መሣሪያዎች፣ የውበትና ቆዳ እንክብካቤ ውጤቶች፣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶች፣ የምግብና የምግብ ነክ የግብርና ምርቶች፣ የአውቶሞቲቭ መለዋወጫዎች፣ የኤሌክትሪክና የቤት እቃዎች በአውደ ርዕዩ እንደሚቀርቡ ገልጸዋል።

በዚህም ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የምስራቅ አፍሪካና ሌሎች የአህጉሪቷ የንግድ ተዋናዮችና የስራ ኃላፊዎች እንዲገኙ ጋብዘዋል።

የኢትዮጵያና የፓኪስታን ጠንካራ አጋርነትና የምስራቅ አፍሪካ ባለግዙፍ ኢኮኖሚና የሃይል አቅራቢ ሀገር በመሆኗ የንግድ ልማት ጉባኤና አውደ ርዕዩን በኢትዮጵያ ለማካሄድ መወሰኑንም ተናግረዋል።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር፥ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የፓኪስታን ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ እንዲያደርጉ ተነሳሽነት እየፈጠረ ነው ብለዋል።

ባለሀብቶቹ በግብርና ማቀነባበር፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በሕክምና እና ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

5ኛው የፓኪስታን አፍሪካ የንግድ ልማት ጉባኤና አውደ ርዕይ በኢትዮጵያና ፓኪስታን መካከል ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አንስተዋል።

የፓኪስታን ንግድና ኢንቨስትመንት ሚኒስትር ባሲጥ ሳሊም ሻህ÷ ለ5ኛው የፓኪስታን-አፍሪካ የንግድ ልማት ጉባኤና አውደ ርዕይ ኢትዮጵያን መርጠናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት አርዓያ የሆነ አስደናቂ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች የምትገኝ ሀገር መሆኗንም ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማም እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ከተማዋን ውብ ገጽታ ያላበሱ አስደናቂ ተግባራት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በፓኪስታን-አፍሪካ የንግድ ልማት ጉባኤና አውደ ርዕይ የአፍሪካ ሀገራት እና የፓኪስታን መንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የንግድ መሪዎችና ባለሃብቶች የሚሳተፉ ሲሆን፥ ዝግጅቱም የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የንግድ ጉባኤ፣ የሁለትዮሽ የንግድ ውይይቶች፣ የመንግስት ለመንግስት የምክክር መድረኮችን ጨምሮ የተለያዩ ሁነቶች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.