የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አዲስ የዲጂታል ኢንተርፕራይዝ አሰራር መሰጠት ተጀምሯል

May 15, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2017(ኢዜአ)፦ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አዲስ ዲጂታል ኢንተርፕራይዝ የተሰኘ አሰራር መሰጠት መጀመሩን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ፍትሃዊ፣ ዘመናዊና ተደራሽ እንዲሆን መንግስት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

ሚኒስቴሩ ባካሄደው ሪፎርም አገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻልና ማዘመን የሚያስችሉ በርካታ ስራዎችን አከናውኗል።


በተለይም ዜጎች ከተቋሙ የሚያገኙትን አገልግሎት ቀላልና ተደራሽ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮችን ማስረጽና ተግባራዊ ማድረግ ዋነኛው መሆኑንም አብራርተዋል።

ይህን ተከትሎ በተቋሙ የሚሰጡ በርካታ አገልግሎቶች ከሰው ንክኪ ነጻ በሆነ መልኩ በቴክኖሎጂ ታግዘው ተደራሽ እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

በፌዴራል ተቋማት በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ የተደረገው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተቋማትን አሰራር ለማዘመን ምቹ እድል እንደፈጠረም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በዚህም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል ሁለቱ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መሰጠት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

አገልግሎቶቹ የውጪ ሀገር ዜጎች የስራ ፍቃድ እና እድሳት እንዲሁም ዲጂታል ኢንተርፕራይዝ የተሰኙ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ዲጂታል ኢንተርፕራይዝ የተሰኘው አገልግሎት እንደ ሀገር አዲስ ስርዓት መሆኑን ጠቁመው አገልግሎቱ ዜጎች በኢንተርፕራይዝ ሲደራጁ ይገጥማቸው የነበረውን የተንዛዛ አሰራር የሚያስቀር ነው ብለዋል።

ቀደም ሲል በኢንተርፕራይዝ የመደራጀት ሒደቱ የበርካታ ተቋማትን በር ማንኳኳት የሚጠይቅ እንደነበር አስታውሰው አካሄዱ መጉላላትን ሲያስከትል እንደነበር ጠቅሰዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል ዘመናዊ አገልግሎት አሰጣጥን ከማረጋገጥ በዘለለ ለተቋም ግንባታ አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

ተቋማት በቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚሰጡት የዘመነ አገልግሎት ለሀገረ መንግስት ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጉልህ በመሆኑ ጠንካራና ዘመን ተሻጋሪ አሰራርን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ለዚህም ቴክኖሎጂን ማስረጽ፣ መተግበርና አሟጦ ጥቅም ላይ ማዋል ዋነኛው ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ አስፈላጊ አገልግሎቶች ወደ ዜጎች እየቀረቡ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ስርዓቱ አገልግሎት አሰጣጡን ከማዘመንና ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ሀገሩን የሚወድና ለሀገሩ እድገት የሚተጋ ትውልድ ለመፍጠር እድል እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

ማዕከሉ ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡና ህዝቡ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.