አዳማ፤ ግንቦት 6/2017(ኢዜአ)፦ የአዳማ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 26 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶች ማምረቱን የልዩ ዞኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጉልላት አበበ ገለፁ።
በልዩ ዞኑ ተመርተው ወደ አውሮፓና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከተላኩ የተለያዩ ምርቶች ከ12 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱም ተገልጿል።
የአዳማ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጉልላት አበበ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት በሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉን ተከትሎ ዞኑ የሪፎርም ስራዎችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
ከለውጥ ስራዎቹ መካከል ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካትና በሽያጭ ሰንሰለት ውስጥ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ 24 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶች ለማምረት ታቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በዞኑ 26 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ተኪ ምርቶችን በማምረት ከእቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል።
ለውጤቱም የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ማበረታቻዎች በአግባቡ በመተግበራቸውና የተለያዩ ማሽነሪዎችን በማስገባት ምርት ሊመረት በመቻሉ መሆኑን አስረድተዋል።
ቀደም ሲል በአልባሳት ስፌት እና ጨርቃጨርቅ ላይ ስናተኩር ከነበረው ባሻገር ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚያገለግሉ ተኪ ምርቶች በስፋት በዞኑ እየተመረቱ ነው ብለዋል።
ከዚህ አንፃር በፊት ከቻይና፣ ከመካከለኛው ምስራቅና ከአውሮፓ ሀገራት ሲገቡ የነበሩና አሁን በዞኑ እየተመረቱ ካሉ ተኪ ምርቶች መካከል የፕላስቲክ ውጤቶች እንዲሁም በኤክስፖርት ደረጃ የሚመረቱ የግድግዳ ቀለሞችና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በስፋት እየተመረቱ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዞኑ የሚገኙ ኩባንያዎች ከውጭ የሚያስገቡትን ጥሬ ግብዓቶችንም በሀገር ውስጥ ምርት እንዲተኩ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በውጭ ምንዛሬ ግኝት ረገድም በዞኑ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ተመርተው ወደ ውጭ ከተላኩ አልባሳትና ጨርቃጨርቅን ጨምሮ ከልዩ ልዩ ምርቶች 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱንም ገልጸዋል።
የአዳማ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለ9 ሺህ ዜጎች ቀጥተኛ የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን 20ሺህ ሰዎች ደግሞ በተዘዋዋሪ የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በልዩ ዞኑ 19 ሼዶችን በመረከብ ሥራ ላይ ከሚገኙ ኩባንያዎች መካከል ሰባቱ የውጭ ሀገር ባለሀብቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአዳማ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ከሚገኙ ኩባንያዎች መካከል የኖርዌይ ጆቱን-ኢትዮጵያ ካምፓኒ ተወካይ ዮሐንስ አለነ በሰጡት አስተያየት ኩባንያው የግድግዳ ቀለሞችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ በስፋት እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር ባለፉት አራት ዓመታት ምርታማነቱን በየዓመቱ በማሳደግ ከውጭ የሚገባውን ተመሳሳይ ምርት በማስቀረት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት መቻሉን አስረድተዋል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025