የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት ገቢን አሟጦ መሰብሰብ ይገባል

May 15, 2025

IDOPRESS

ቴፒ፤ ግንቦት 6/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት ገቢን አሟጦ መሰብሰብ እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት አስታወቀ።


በሸካ ዞን በህብረተሰቡ ተሳትፎ ገቢና ልማት ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ያተኮረ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በቴፒ ከተማ ተካሂዷል።


በመድረኩ ላይ የተገኙት በክልሉ ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ የኋላሸት በላይነህ እንደገለጹት በክልሉ ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል በቅንጅት እየተሠራ ነው።


የልማት ሥራዎች የሕዝብን ፍላጎት መሠረት አድርገው እንዲተገበሩ ምክር ቤቱ ከአስፈጻሚ አካላት ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።


በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ገቢን አሟጦ የመሰብሰብ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።


ልማትን ለማፋጠን የክልሉን ሰላም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸው፣ መድረኩ ልማትና ገቢ የተሳሰሩ መሆናቸውን ለህብረተሰቡ ለማስገንዘብ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።


ህብረተሰቡ ግብሩን በአግባቡ ከመክፈል ባለፈ የልማት ተሳትፎውን በማጠናከር የበኩሉን እንዲወጣም አስገንዝበዋል።


የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሕይወት አሰግድ በበኩላቸው የክልሉን ወጪ በራስ አቅም ለመሸፈን የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የኅብረተሰቡ ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።


በተለይም ከተረጂነት መውጣት ገቢ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቅሰው፣ ግብርን በታማኝነት በመክፈል ልማትን መደገፍ ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል ብለዋል።


የመንግሥት ገቢ በትክክል ተሰብስቦ ለልማት እንዲውልም ህብረተሰቡ በየደረጃው ሕገወጥ አሠራርን መታገል እንዳለበትም አሳስበዋል።


በቴፒ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ የተገኙት የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ሰላምና ልማጥን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ገለጻ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.