የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ፓርኩ ወደ ውጭ ከላከው የአቮካዶ ዘይት ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ባለይ የውጭ ምንዛሬ አስገኘ

May 19, 2025

IDOPRESS

ሀዋሳ፤ግንቦት 8/2017 (ኢዜአ)፦ይርጋዓለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ውጭ ከላከው የአቮካዶ ዘይት ምርት ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘቱን የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለፀ።


የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኃይሉ ዬቴራ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ገቢው የተገኘው ፓርኩ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ወደውጭ ከላከው የአቮካዶ ዘይት ምርት ነው።


ፓርኩ የአቮካዶ፣የወተት፣ የማርና የቡና ምርቶችን እንደሚያቀነባብር ጠቅሰው፥በዚህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ከመተካት ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።


በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከፓርኩ ወደ ውጭ ከተላከ የአቮካዶ ዘይት ምርት ከ1 ሚሊዮን 984 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር መገኘቱንም ገልጸዋል።


ከዚህ በተጨማሪ በማር፣በወተትና በቡና ከ232 ሺህ ዶላር በላይ ግምት ያላቸው ተኪ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረቡንም አስረድተዋል፡፡


ፓርኩ ሥራ ከጀመረ አምስት ዓመታትን እንዳስቆጠረ ያስታወሱት አቶ ኃይሉ፣ በእነዚህ ዓመታት 14 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ተኪ ምርት ማምረቱን ገልጸዋል።


ባለፉት ዓመታት በፓርኩ ወደ ውጭ ከተላከ የአቮካዶ ዘይትም 19 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት መቻሉን አስረድተዋል።


በአሁን ወቅት በፓርኩ ስምንት ኩባንያዎች ወደ ሥራ ገብተው ተኪና የኤክስፖርት ምርት እያመረቱ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ኃይሉ፣ ውል ገብተው ወደ ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ ያሉ 25 ኩባንያዎች እንዳሉም አስታውቀዋል።


እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ በአምስት ዓመታት በፓርኩ ውስጥ ባሉ ኩባንያዎች በቅጥር፣የተሻሻለ የአቮካዶ ዝርያ ችግኝ በማፍላት፣ በግብአት አቅራቢነት እና በሌሎች ዘርፎች 25 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ ሥራ ዕድል ተፈጥሯል።


በፓርኩ የጎልደን አቦካዶ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የምርት አቅርቦት ክፍል ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ቴጎ፥ ባለፉት ወራት ፋብሪካው ወደ ጣሊያንና ሌሎች ሀገራት 80 ሺህ ኪሎ ግራም ድፍድፍ የአቮካዶ ዘይት መላኩን ተናግረዋል፡፡


ፋብሪካው ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር አርሶ አደሩ ከእርሻ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርት አሰባሰብ ድረስ ዘመናዊ አሰራርን እንዲከተል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የማስገንዘብ ሥራ እንደሚያከናውንም አስታውቀዋል።


የፋሚሊ ማር ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ንጉሴ በበኩላቸው፥ ፋብሪካው የተጣራ ማርና ሰም በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ይገኛል።


በቀጣይ አስፈላጊውን ሂደትና መስፈርት በማሟላት ምርቱን ወደተለያዩ የውጭ ሀገራት ለመላክ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።


እንደ አቶ ዘሪሁን ገለጻ፥ፋብሪካው ባለፉት አራት ወራት ውስጥ 4 ነጥብ 5 ቶን የተጣራ የጫካ ማር አምርቶ ለገበያ አቅርቧል።


በጠቅላላው በ6 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ይርጋዓለም የተቀኛጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ294 በላይ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.