የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ማዕከሉ የሚያከናውነው የጥራት ቁጥጥር ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ለምታደርገው ጥረት አጋዥ ነው

May 21, 2025

IDOPRESS

ግንቦት፤ ግንቦት 12/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የእንስሳት ምርትና ግብዓት ጥራት ምርመራ ማዕከል የሚከናወኑ ተግባራት ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የግብርና ግብዓት፣ቴክኖሎጂ፣ ምርትና አገልግሎት ጥራት እንዲሁም ደህንነት የማረጋገጥና የመቆጣጠር ተግባርን በዋነኝነት ያከናውናል፡፡


ማዕከሉ የስጋ፣ ወተት፣ ማርና እንቁላል ጥራት፣ ተስማሚነትና ደህንነትን የማረጋገጥ እንዲሁም የእንስሳት መድኃኒት ጥራት፣ ፈዋሽነትና ደህንነት የማረጋገጥ ስራዎችን ይሰራል።

በማዕከሉ የፊዚኮ ኬሚካል ጥራት ምርመራ ላቦራቶሪ መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር በላቸው ባጫ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የእንስሳት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምርና ጥራቱ ተጠብቆ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን የምርት ጥራት ምርመራ ወሳኝ ነው፡፡

በመሆኑም ማዕከሉ በእንስሳት ምርትና ግብዓት ጥራት ጉድለት ምክንያት ሊመጡ የሚችሉ የጤና ችግሮችን ለመለየት እና ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከውጭ የሚገቡ የእንስሳት መድኃኒቶች አገልግሎት ላይ ከመዋላቸው በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን የጥራት መስፈርት ማሟላታቸውን ማረጋገገጥ ከተሰጡት ተልዕኮዎች አንዱ ነው፡።

ከዚህም በተጨማሪ ከሀገር የሚወጡ የእንስሳት ምርቶች ጥራትና ደህንነት የማረጋገጥ ተግባርም በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።


በማዕከሉ የጥራት ቁጥጥር ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ዘሪሁን አበጋዝ በበኩላቸው ማዕከሉ የሚያካሄዳቸው ምርምሮችና የሚከተላቸው የምርመራ ዘዴዎች ዓለም አቀፍ ደንቦችና ህጎችን የተከተሉ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡

ዘመኑን የዋጁ ላቦራቶሪዎችና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከዓለም አቀፍ የጥራት መስፈርቶች አኳያ ስራቸውን እያከናወኑ እንደሚገኙ አንስተዋል።

ማዕከሉ እያደረገ ያለው የጥራት ቁጥጥርና ምርመራ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑን አስታውቀዋል።


በማዕከሉ የማይክሮ ባይሎጂ ላቦራቶሪ ዘርፍ ኤክስኪዩቲቭ ኦፊሰርና የማዕከሉ ኃላፊ ተወካይ ዶክተር ናርዶስ ተፈራ በበኩላቸው፤ ማዕከሉን በቴክኖሎጂ፣ በሰለጠነ የሰው ሃይልና በግብዓት ማደራጀት በመቻሉ የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንንም አጠናክሮ ለማስቀጠልና የማዕከሉን የምርምር አድማስ ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡


የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሀሚድ ጀማል፤ የእንስሳት ጤንነትን በማስጠበቅ ጥራት ያለውና በገበያ ተፈላጊ የሆነ ምርት እንዲመረት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.