አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረጉ የልማት ኢኒሼቲቮች የኢኮኖሚ ዕድገቱን ከማሳለጥ ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ተናገሩ።
20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት በሥራ ላይ የተመሰረተ የባለሙያዎች አህጉራዊ ስብሰባ "የማይበገር ማህበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች" በሚል መሪ ሀሳብ በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
በስብሰባው የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ተገኝተዋል።
ከስብሰባው ጎን ለጎንም ሀገራት በሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ ያላቸውን ተሞክሮ የሚለዋወጡበት የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ አካታች የኢኮኖሚ ሥርዓት በመዘርጋትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ረገድ ስኬታማ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።
የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ለስራ ዕድል ፈጠራው ያለውን ጉልህ ሚና በማጤንም መንግሥት የግሉን ዘርፍ በማበረታታት ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ሁኔታዎችን ማመቻቸቱንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ ቀደም በአመዛኙ በግብርና ላይ የተመሰረተ የሥራ ዕድል ፈጠራ እንደነበር አስታውሰው፤ የብዝሃ ኢኮኖሚ አሰራርን በመከተል ከግብርና ባሻገር በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እንዲሁም በዲጂታል ኢኮኖሚ የሥራ ዕድል ፈጠራውን የሚያሳልጡ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብርም የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ ኢትዮጵያ ቁልፍ አጀንዳ ማድረጓን ገልጸው፤ ይህም የሥራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴው ላይ አበረታች ውጤቶች እንዲገኙ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ለአብነት ጠቅሰው፤ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በግንባታው መስክ የተገኘው ውጤት ተጠቃሽ መሆኑን አስረድተዋል።
በሀገሪቱ ወደ ሥራ የገቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል ነው ያሉት።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ደኤታ ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በሴፍቲኔት መርሃ ግብር በገጠርና በከተማ የሥራ ዕድል ዜጎች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።
ክህሎት መር ፖሊሲ አሰራርን በመተግበርም የተቋማት ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የሰለጠነ የሰው ኃይል ወደ ሥራ እንዲገባ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ፍሬ እያፈሩ መሆኑንም አንስተዋል።
በተለይም በዲጂታል መስክ ስታርታፖችን በመደገፍ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ በተዘረጋው ማበረታቻ ሥርዓት በርካታ ስታርታፖች ምህዳሩን እየተቀላቀሉ ነው ብለዋል።
በክህሎት ልማት ዘርፍ ቀጣናዊ ትብብሮችን በማጠናከር ለጋራ ብልጽግና ትኩረት ተሰጥቷል ሲሉም ተናግረዋል።
በዓለም የሥራ ድርጅት የልማትና ኢንቨስትመንት ቅርንጫፍ የቅጥር ፖሊሲ መምሪያ ኃላፊ ሚቶ ቱስካማቶ እንዳሉት፤ እያደገ የመጣው የመሰረተ ልማት ግንባታ ተገቢው የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ሀገራት የተሻለ አሰራር ቀርጸው ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
በሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ ያሉ መልካም ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ በተለይም ተጋላጭ የሆኑ የኀብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ርብርብ ይጠይቃል ነው ያሉት።
ስብሰባውን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከዓለም የሥራ ድርጅት(ILO) ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን፤ ከግንቦት 11 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025