የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በመጪው ክረምት የእረፍት ጊዜ የኮደርስ ስልጠናን በመከታተል የዲጂታል ክህሎታችንን ለማሳደግ ዝግጁ ነን-ተማሪዎች

May 27, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ግንቦት 18/2017(ኢዜአ)፦በመጪው ክረምት በሚኖራቸው የእረፍት ጊዜ የኮደርስ ስልጠናን በመከታተል የዲጂታል ክህሎታቸውን ለማሳደግ ዝግጁ መሆናቸውን የ12ተኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ገለፁ።

የአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አዋሌ መሀመድ በበኩላቸው እስካሁን 130 ሺህ ዜጎች የኮደርስ ስልጠና ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ የስልጠና ተነሳሽነት "ትውልድ ይማር፣ትውልድ ይሰልጥን፣ከዓለም ጋር ይፎካከር" በሚል እሳቤ ዲጅታል ክህሎትን የተላበሰ ብቁ ዜጋ ለማፍራት እየተተገበረ ይገኛል፡፡

ተነሳሽነቱ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ዜጎች በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ዳታ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል እውቀት እንዲጨብጡ የሚያስችል ነው።

በኮከበ ፅባህ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ የ12ተኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት የኮደርስ ስልጠና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ ነው።

ተማሪ አቤኔዘር ዘገየወርቅ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በሰመር ካምፕ የኮደርስ ስልጠና በመከታተል የምስክር ወረቀት ማግኘቱን ተናግሯል።

የኮደርስ ስልጠናን እየተከታተለ እንደሚገኝ የጠቀሰው ተማሪ አብርሃም ሰላምነህ በበኩሉ፥ ስልጠናው የተለያዩ የትምህርት እድሎችን ለማግኘት ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጿል።

ስልጠናው ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘት የሚያስችል፣ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግና ተጨማሪ እድሎችን የሚከፍት በመሆኑ በእረፍት ጊዜው ለመከታተል ዝግጁ መሆኑን የገለፀው ደግሞ ተማሪ ባሴል ደረጀ ነው።

ተማሪ አማኑኤል ታሪኩ በበኩሉ ከፈተና በኃላ በሚኖረው የእረፍት ጊዜ ወደቀጣይ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ተግባራትን ለማከናወን እንዳሰበ ገልጾ የኮደርስ ስልጠና የዕቅዱ አካል መሆኑን ተናግሯል።

ተማሪዎች በመጪው ክረምት የእረፍት ጊዜያቸውን ስልጠናውን በመከታተል ራሳቸውን ማብቃት ይገባል ያለችው ደግሞ ተማሪ ኮሊያ ገረመው ናት።

በኮደርስ ስልጠና የተካተቱ ኮርሶች ለመጪው ዘመን አስፈላጊ እውቀት የሚያስጨብጡ በመሆናቸው በእረፍት ጊዜ ክህሎትን ማዳበር እንደሚገባ ተማሪ ሰሎሜ ታደሰ ገልጻለች።


የአዲስ አበባ ከተማ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አዋሌ መሀመድ እንዳሉት፥ የኮደርስ ስልጠና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት እንዲሁም ፈጠራና ስታርትአፕን የሚያበረታታ ነው።

በመዲናዋ እስካሁን 218 ሺህ በላይ ዜጎች የኮደርስ ስልጠናን እየተከታተሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ 130 ሺህ ያህሉ ማጠናቀቃቸውንም አንስተዋል።

በቀጣይም በኮሌጆች፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና በክረምቱ ወቅት ደግሞ የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች ስልጠናውን እንዲከታተሉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.