የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ሀገር በቀል የልማት እሳቤ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎትን በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ፈጥሯል

May 27, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የልማት እሳቤ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎትን በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም መፍጠሩን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔና ሴክተር ክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ታደሰ ገለጹ።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ንቅናቄ ስትራቴጂክ ማዕቀፎች ትግበራ ላይ ለፌደራል፣ ለክልልና ለከተማ አስተዳደሮች ባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

በአፍሪካ ልህቀት አካዳሚ እየተካሄደ የሚገኘው የምክክር መድረክም የአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን፣ የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ትብብር እንደተዘጋጀ ተገልጿል።


በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔና ሴክተር የክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ መንግስት የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን በራስ አቅም ማረጋገጥ የሚያስችል ታሪካዊና ጨዋታ ቀያሪ ውሳኔዎችን አሳልፏል ብለዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን ሀገር በቀል የብዝኅ ኢኮኖሚ የሪፎርም እርምጃዎች ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ የተዘጋጁ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎችም የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትና ፍላጎት ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አቅም እየፈጠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን አምራች ዜጋ፣ የተቸራትን ምቹ አየር ጠባይና የተፈጥሮ ጸጋ በመጠቀም የሀገርን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ኢትዮጵያ በወሰደችው ሀገር በቀል ሁሉ አቀፍ የማሻሻያ እሳቤ ስኬቶችም የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ማሳካት ማሳያዎች መሆናቸውን አንስተዋል።


በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እንዲሁም በሌማት ትሩፋት በእንስሳት፣ በሰብልና አትክልትና ፍራፍሬ የተገኘው ውጤት ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በኢንዱስትሪ ዘርፍ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና ቴክኖሎጂ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነት ፓኬጅ የሆኑትን የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ፣ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ መጠባበቂያና የዕለት ደራሽ ክምችት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የክምችት መጋዘኖች፣ የቅጽበታዊ አደጋዎች አገልግሎትና የቤተሰብ ሀላፊነት እንዲሁም የማህበረሰብ አጋርነት ጉዳዮችን ለማሳካት በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) በበኩላቸው ተረጂነት ኢትዮጵያን የማይመጥን ከኢትዮጵያውያን ባህልና ልምድ የተቃረነ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን በአርበኝነት መንፈስ በቁርጠኝነትና በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.