የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ዘመን ተሻጋሪ ተግባር መሆኑ ተመላከተ

May 28, 2025

IDOPRESS

ወልዲያ፤ ግንቦት 19/2017(ኢዜአ)፦ በወልዲያ ከተማ በግንባታ ላይ ያለው የኮሪደር ልማት የነገውን ትውልድ ታሳቢ ያደረገና ዘመን ተሻጋሪ ተግባር መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የአዲስ አበባን የኮሪደር ልማት ሥራ ተሞክሮ ወደ ክልሎች በማስፋት የክልል ከተሞችን ውብና ሳቢ ከማድረግ ባሻገር ለነዋሪዎቻቸው የተመቹ፤ ለጎብኚዎችም ተመራጭ እንዲሆኑ የተጀመረው ስራ ውጤት እየተመዘገበበትም ይገኛል።

በወልዲያ ከተማ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት በታለመለት ጊዜና ጥራት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር ገልጿል።

የከተማዋን ገፅታ በመቀየር ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ተመራጭ እንዲሁም የምርምርና የሥራ ዕድል ፈጠራ ማዕከል የማድረግ ስራ እየተሰራመሆኑም ተመላክቷል።

በወልዲያ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማትም ከተማዋን በተጨባጭ እየለወጠ ያለ የልማት ስራ ከመሆኑም ባሻገር ዘመን ተሻጋሪ መሆኑን ነው ነዋሪዎቿ የመሰከሩት።

በወልዲያ ከተማ ነዋሪ አቶ እንድሪስ አባቡ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተማዋ ጥንታዊ በመሆኗ ያሏት መሰረተ ልማቶች ዘመኑን አይመጥኑም።

በተለይም የመንገዶቹ መጥበብ ተሽከርካሪ፣ ሰውና እንስሳት እየተጋፉ የሚሄዱበት በመሆኑ ለአደጋ መንስኤ እንደነበር አስታውሰዋል።

በተለይም ለአቅመ ደካሞች፣ ማየት ለተሳናቸውና ለህሙማን እንቅስቃሴ ትልቅ ፈተና እንደነበርም ነው የገለጹት።


በአሁኑ ወቅት በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ገና ሳይጠናቀቅ የነበሩ ችግሮች እየተፈቱ መምጣታቸውንና የነገውን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ የልማት ሥራ በመሆኑም ተደስተናል ብለዋል።

በወልዲያ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከሌሎች ከተሞች ጋር እኩል የሚያራምደን ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ተመስገን አንዳርጌ ናቸው።

ዓለም የደረሰበት ስልጣኔ ላይ ለመድረስ ለአዳዲስ አስተሳሰብ ተገዢ ልንሆን ይገባል ያሉት አስተያየት ሰጪው ተግባሩን መደገፍ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የኮሪደር ልማቱ ሲጠናቀቅ ውብና ለኑሮ ምቹ የሆነች ወልዲያን የማየት ጉጉት እንዳደረባቸውም ገልፀዋል።

በኮሪደር ልማቱ መጀመር የሥራ እድል ተፈጥሮለት ተጠቃሚ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የግንባታ ባለሙያው ወጣት ብርሃኑ መንጌ ነው።

ተወልጄ ባደኩባት ከተማ በሙያዬ አገልግዬ ተጠቃሚ በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ ያለው ወጣቱ ስራው በጊዜና በጥራት እንዲከናወን ሙያዊና ሀገራዊ ግዴታዬን እየተወጣሁ ነው ብሏል።

የወልዲያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው የከተማዋን የኮሪደር ልማት የማፋጠን ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በከተማዋ ለመገንባት ከታቀደው 16 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ ውስጥ ከአዳጎ አደባባይ እስከ ሙጋድ ያለው የአንድ ኪሎ ሜትር መንገድ ስራ በቀጣይ ወር ግንባታው ይጠናቀቃል ብለዋል።

ሌላው ከሙጋድ እስከ ጎንደር በር ያለው አንድ ኪሎ ሜትር የአፈር ሙሌት ስራ እየተሰራ በመሆኑ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በኮሪደር ልማቱ ከአካባቢያቸው ለተነሱ ሰዎች የካሳ ክፍያና ምትክ ቦታ ማስረከቡንም ተናግረዋል።

ለኮሪደር ልማቱ ስኬት መላው የከተማዋ ነዋሪ እያሳየ ላለው ቀና ትብብር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.