የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

አፍሪ ኤግዚም ባንክ በኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል

Jun 3, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 25/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት (አፍሪ ኤግዚም) ባንክ በኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ የሚያደርገውን ድጋፍ የበለጠ እንዲያሳድግ አስቻይ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ።

በአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ የተዘጋጀ በኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንት ዕድገት ላይ ያተኮረ ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ መክፈቻ ላይ የብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ፍቃዱ ድጋፌ እንደገለጹት ባንኩ የኢትዮጵያን የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች በመደገፍ በኩል ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።


ባንኩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከ14 የግል ባንኮች ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን የበለጠ እንዲያጠናክር እንፈልጋለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ያካሄደችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ባንኩ በኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንት ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ የበለጠ እንዲያጠናክር አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን አንስተዋል።

ባንኩ በኢትዮጵያ ከውጭ ለሚገቡ ስትራቴጂክ ሸቀጦች ዋስትና በመስጠትም እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የባንኮችን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማቃለሉ ከባንኩ ጋር በጋራ የመስራት ዕድላቸውን ማሳደጉንም ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ አፍሪ ኤግዚም ባንክ ለኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ባንኮች የተሻለ ድጋፍ እንዲያደርግ የሚያስችል መሆኑንም ነው የጠቀሱት።


የአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት(አፍሪ ኤግዚም) ባንክ የደንበኞች ግንኙነት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ኢሪክ ሞንቹ ባንኩ የንግድ ልውውጥን ለማሳለጥና የኢንዱስትሪ ልማትን ለማፋጠን የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገቡ ካሉ ግንባር ቀደም ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቅሰው የተገበረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በኢንዱስትሪው ላይ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

የዋጋ ግሽበትን ከመቀነስ አኳያም የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።


የባንክ ሥራ አዋጁ መሻሻል ለፋይናንስ ዘርፋ ምቹ የስራ ከባቢ በመፍጠር በኩል ጉልህ ድርሻ እንዳለውም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ለባንክ ሥራ ምቹና አስተማማኝ መሆኗን ጠቅሰው፤ ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ እንድትሆን ባንኩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።


የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ህሊና በላቸው፣ ባንኩ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ የበለጠ እንዲያጠናክር በጋራ መስራት የሚያስችሉ ዕድሎች መፈጠራቸውን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት(አፍሪ ኤግዚም) ባንክ በአፍሪካ ከአፍሪካ ውጪ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ በባለብዙ ወገን ትብብር የተቋቋመ ሲሆን ኢትዮጵያም እኤአ ከ1994 ጀምሮ የባንኩ አባል ሆናለች።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.