ባሕር ዳር፤ ግንቦት 26/2017 (ኢዜአ)፡- በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሰፈነው ሰላም የልማት ስራዎችን ይበልጥ ለማሳለጥ የሚያስችል ምቹ መደላድል መፍጠሩን የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ተናገሩ።
በከተማው እየተከናውኑ በሚገኙ ዋና ዋና የልማት ኘሮጀክቶች አፈፃፀም ዙሪያ በየደረጃው የሚገኙ አመራር አባላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ዛሬ በባሕርዳር ተካሄዷል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በወቅቱ እንደገለጹት፤ ሕዝቡን በማሳተፍ በተከናወነው ሕግ የማስከበር ስራ ሰላምን ማፅናት ተችሏል።
በከተማዋ የሰፈነው ሰላም የቱሪስቶችን ፍሰት ከመጨመር ባለፈ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት ይበልጥ አሳልጦ መስራት የሚያስችል ምቹ መደላድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
ለሰላሙ መፅናትና ልማት ስራዎች ሕብረተሰቡ በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በእውቀቱ እያደረገ ያለው ያልተቆጠበ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተው፤ በየደረጃው ያለው አመራርም የሕዝብን የልማት ፍላጎት መሰረት በማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአስተዳደሩ ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ተሻገር አዳሙ በበኩላቸው፤ በከተማው የሕዝብን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በዚህም በመጀመሪያውና በሁለተኛው ምዕራፍ 22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ ለማከናወን ከታቀደው ውስጥ የመጀመሪያውን ምዕራፍ የ3 ኪሎ ሜትር ማጠናቀቅ መቻሉን ጠቅሰዋል።
የኮሪደር ልማቱ ስማርት ባህርዳርን እውን በማድረግ የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማትም መጀመሩን አንስተዋል።
እንዲሁም የ22 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፋልት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
የከተማው ነዋሪ ህንፃዎችን በራሱ ወጪ በማስዋብ፣ ለልማት የሚፈለጉ አካባቢዎችን በፈቃደኝነት በማንሳት ለልማቱ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየቱንም አብራርተዋል።
''የከተማው መሰረተ ልማትና የኮሪደር ልማቱ በዕቅድና አፈፃፀሙ ከሕዝብ ጋር በመወያየትና በመግባባት እየተከናወነ ነው'' ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ የከንቲባ አደረጃጀት አማካሪ አቶ ጌታቸው ግዛቸው ናቸው።
በከተማው በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ከሕብረተሰቡ እስካሁን ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
መድረኩ ለልማት ስራዎች ሕብረተሰቡ ማድረግ ያለበትን ሁለንተናዊ እገዛ በንቅናቄ አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልበት ዙሪያ ውይይትና የቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቋል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025