የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ጥቅል የነዳጅ ድጎማን በማስቀረትና ለሲሚንቶ ኢንቨስትመንት ፈቃድ በመስጠት የተረጋጋ ገበያ መፍጠር ተችሏል - ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)

Jun 5, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት ጥቅል የነዳጅ ድጎማን በማስቀረትና ለሲሚንቶ ኢንቨስትመንት ፈቃድ በመስጠት የተረጋጋ ገበያ መፍጠር መቻሉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና ገቢዎች ሚኒስቴር "ለሁለንተናዊ ብልፅግና የንግዱ ማህበረሰብ ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ምክክር አድርገዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ መንግስት የሀገሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥ ብዝሀ ዘርፍ ኢኮኖሚ ልማትን ተግባራዊ በማድረግ በየዘርፉ ስኬቶችን እያስመዘገበ ነው።

በኢትዮጵያ ለተመዘገቡ ሁለንተናዊ እድገቶች የንግዱ ማህበረሰብ ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዘርፉ ተዋንያን ተገቢውን እውቅና እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

የንግዱ ዘርፍ እሴት የተጨመረበት ምርትና አገልግሎትን ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ በማድረግ በኩልም የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።


የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ትብብር በኢኮኖሚ የዳበረች ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፤ ግንኙነቱ በጠንካራ መሰረት ላይ መቀመጥ ይኖርበታል ብለዋል።

በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደዚህ ዓይነት የምክክር መድረኮች ወሳኝ መሆናቸውንም አንስተዋል።

የንግዱን ዘርፍ ችግሮች በመፍታት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የንግድ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ገልጸው ከ63 ዓመት በላይ የቆየው የንግድ ህግ እንዲሻሻል ተደርጓል ብለዋል።

ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ የነበሩ የወጭ፣ የገቢ፣ የጅምላና ችርቻሮ ንግድ ክፍት እንዲሆኑ የሚያስችል የኢንቨስትመንት ደንብ ማሻሻያ መደረጉንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ሲዳርጋት የቆየውን ጥቅል የነዳጅ ድጎማ በማስቀረት የተደራጀ ግብይትና ስርጭት መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

መንግስት ከግንባታ ዘርፉ ማደግ ጋር ተያይዞ እየጨመረ የመጣውን የሲሚንቶ ፍላጎት ለማሟላት ለሲሚንቶ ልማት ፈቃድ መስጠቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት በገበያ እንዲመራ በማድረግ በኩንታል እስከ 2ሺህ 400 ብር የነበረው ሲሚንቶ ዛሬ ላይ ከግማሽ በላይ መቀነስ የሚያስችል ስራ መሰራቱን በመግለጽ፡፡

የሀገር ውስጥ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑበት ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰው፤ የመንግስትን አገልግሎት ቀልጣፋና ምቹ ማድረግ የሚያስችል የአሰራር ማሻሻያ ተደርጓል ብለዋል።

በህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ በተሰማሩ አካላት ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ሊደርስ ይችል የነበረውን አደጋ ማስቀረት መቻሉንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ከስድስት ዓመታት በፊት ከሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር በታች የነበረው የውጭ ንግድ ዘርፍ አፈፃፀም በበጀት ዓመቱ አስር ወራት ብቻ ከስድስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።

መንግስት ኢትዮጵያን የዓለም ንግድ ድርጅት አባል በማድረግ የንግዱን ማህበረሰብ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ በጊዜ የለኝም መንፈስ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መጪው ዘመን ይዞት የሚመጣውን ዕድል ለመጠቀም አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ በተምሳሌትነት የሚጠቀሱ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ማፍራት መጀመሩን ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያ እድገትና ልማት የወጭ ንግድ ተወዳዳሪነት ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፣ የግሉ የንግድ ዘርፍ ተዋንያን የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አሰራሮችን በማወቅ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የንግዱ ዘርፍ ለኢትዮጵያ ብልጽግና የሚጫወተውን ሚና ለማሳደግ ለህብረተሰቡ ወቅቱንና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን እርካታ ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.