የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ፣ የሚጨበጥ እና የሚዳሰስ ለውጥ አለ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

Jun 6, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ፣ የሚጨበጥ እና የሚዳሰስ ለውጥ አለ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ መንግስት የኑሮ ውድነትን ለማስተካከል እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የዋጋ ንረት ሁኔታ የተከማቸ መዋቅራዊ ችግሮች ፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ክስተቶች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ፈተናዎች ተዳምረው የዜጎችን ኑሮ እየፈተነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

መንግስት የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ስብራቶች ለመጠገን የሚያስችሉ ሁሉን አቀፍ የማሻሻያ ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል።

በሪፎርሙ አማካኝነት በኢኮኖሚው ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ መመዝገቡን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢኮኖሚው ዘርፍ ከተገኘው ስኬት መካከል የወጪ ንግድን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከ1984 እስከ 1998 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በወጪ ንግድ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ብቻ ማግኘቷን አስታውሰው በዚህ ዓመት ብቻ ከኤክስፖርት ከ8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ታገኛለች ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

የዋጋ ንረቱን ከነበረበት 34 በመቶ ዘንድሮ 13 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ማለቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገቢ፣ ድህነት ቅነሳ፣ ውዝፍ እዳ ከአጠቃላይ ጥቅር ዓመታዊ ምርት አንጻር መቀነሱ ኢትዮጵያ ከዋጋ ንረት እያገገመች ለመሆኗ ማሳያ ነው ብለዋል።

በተለያዩ መስኮች የተገኙ ለውጦች ቀጣዩ ትውልድ የሚረከበውን እዳ በመቀነስ የተሻለ ሀገር እንዲረከብ የሚያስችል መሰረት የጣለ መሆኑንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ከበሽታዎቿ እያገገመች በመዳን መንገድ ላይ ትገኛለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን ለማድረግ ያለመታከት መስራት እና መድከም እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል።

የተገኘውን ለውጥ ማጽናት እና ማስቀጠል የሁሉም ወገን የጋራ ኃላፊነት እንደሆነም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.