የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የኢትዮጵያ መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰዱ ሀገሪቷን ወደ ፊት እንድትጓዝ አስችሏል-አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ

Jun 9, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ግንቦት 29/2017 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ መንግስት ደፋር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰዱና ሁኔታዎችን በመቀየሩ ሀገሪቷን ወደፊት እንድትጓዝ ማስቻሉን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ገለፁ።


በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ያለው ንግድ እና ኢንቨስትመንት እያደገ መምጣቱንም ገልጸዋል።


በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤የኢትዮጵያ መንግስት በድፍረት የወሰዳቸው እርምጃዎች ሀገሪቷ ላይ ጠቃሚና ትርጉም ያላቸው ለውጦች አምጥቷል።


ከማሻሻያዎቹ መካከል የውጭ ምንዛሪ ተመን አንዱ መሆኑን አስታውሰው፤ይህ ማሻሻያ በመደረጉ ለበርካታ ዓመታት ያልታየ የውጭ ምንዛሪ ገበያ መረጋጋት መከሰቱን ጠቁመዋል።


የኢትዮጵያ መንግስት ቁልፍ ውሳኔዎችን በማሳለፉ የተገኙ ለውጦች መኖራቸውን ያመለከቱት አምባሳደሩ፤ በዚህም የመንግስትን ጥረት አድንቀዋል።


በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ያለው ንግድ እና ኢንቨስትመንት እያደገ መምጣቱን የገለጹት አምባሳደር ማሲንጋ፤ በቀጣይም በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማስፋፋት ፍላጎት መኖሩን ተናግረዋል።


ኢትዮጵያ ሰፊ የወጪ ንግድ አቅም እንዳላት ያብራሩት አምባሳደሩ፤ በተለይም የቡና፣ ሻይ፣ ጤፍ፣ አበባ እና የማዕድን ሀብቶችን ወደ አሜሪካ በመላክ የውጭ ምንዛሬ የማግኘት አቅም እንዳላት ጠቁመዋል፡፡


ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የሚገድብ የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ውስጥ ስትንቀሳቀስ መቆየቷን አውስተው፤አሁን ያለው መንግስት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የወሰደው የፖሊሲ እርምጃንም አድንቀዋል።


በአሁኑ ወቅት ቡናን ጨምሮ ወደ አሜሪካ የሚላኩ ምርቶችን ለማስፋት ትልቅ ዕድል መኖሩን ጠቁመው፤እነዚህን ዕድሎች ለማስፋትም ከኢትዮጵያ መንግስት እና የንግድ ማህበረሰብ ጋር በጋራ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡


በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለው ዘላቂ ትብብር ያደነቁት አምባሳደር ማሲንጋ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ አጋርነት የሚያጎላ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።


በተጨማሪም አሜሪካ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ የሚገነባውን አውሮፕላን ማረፊያ በማልማት ረገድ ዕድሎች ለማየት በንቃት ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.