የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በዲላ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ውብና ጽዱ ከማድረግ ባለፈ የተለያዩ የስራ ዕድሎችን እየፈጠረ ነው-ነዋሪዎች

Jun 9, 2025

IDOPRESS

ዲላ፤ግንቦት 30/2017 (ኢዜአ)፦በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ውብና ጽዱ እንዲሁም ለቱሪዝም ምቹ ከማድረግ ባለፈ የተለያዩ የስራ ዕድሎችን እየፈጠረ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገልፀዋል።


በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ እየተገነባ ያለውን የ10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።


በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።


ከዲላ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ኢዮብ መንግስቴ ለኢዜአ እንደገለጸው፥ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተመርቆ ያለስራ መቆየቱን ተናግሯል።


በኮሪደር ልማቱ የሚከናወኑ መሰረተ ልማቶች የከተማውን ውበት ከመጨመር ባለፈ ለሌሎች ነዋሪዎች የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን መፍጠሩን ጠቁሟል።


የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ በተገነቡ ሱቆች ለህብረተሰቡ የካፌ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሶ፣ይህም ሰርቶ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረለት ተናግሯል።


በኮሪደር ልማቱ የተከናወኑ የእግረኛ መንገዶች እና የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ከተማዋ ተጨማሪ ውበትና ሳቢ ዕይታ እንዲኖራት እያደረጉ መሆናቸውን የገለጸው ደግሞ ወጣት ሲሳይ ስዩም ነው።


በዚህም እሱን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች በለሙ አካባቢዎች ፎቶግራፍ በማንሳት ሥራ ተሰማርተው ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን ተናግሯል።


የፎቶ ግራፍ ማንሳት ሥራው የሰዎችን ትውስታ ከማስቀረትና የከተማዋን ገጽታ ከማስተዋወቅ ባለፈ ጥሩ የገቢ ምንጭ እንደሆነለትም ገልጿል።


ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ክብሩወሰን ተፈራ በበኩላቸው፥ በኮሪደር ልማት ስራው እውን የሆነው የከተማው መብራት ጨለማን ተገን በማድረግ ከሚፈፀሙ ወንጀሎች እንደታደጋቸው ተናግረዋል።


በሌላም በኩል የኮሪደር ልማት ስራው በከተማው የመዝናኛ ስፍራዎች አማራጭን ያሰፋ መሆኑንም አመልክተዋል።


የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፥ በከተማዋ 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው።


ከዚህ ውስጥ የ7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትሩ ግንባታ ሥራ ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃ መሆኑንና ቀሪውንም በታቀደለት ጊዜ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን መግቢያ በር ጨምሮ የእግረኛና የሳይክል መንገድ፣የመናፈሻ ሥፍራ፣የመንገድ ዳር መብራትና ለሥራ ፈጠራ የሚሆኑ ካፌዎችና ሱቆችን አካቶ እየተገነባ መሆኑን አስረድተዋል።


ያረጁ አካባቢዎችን መልሶ ማልማት እና በሦስት ምዕራፎች የሚከናወን የ22 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራ የኮሪደር ልማቱ አካል መደረጉንም አንስተዋል።


የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን እድገት ከማፋጠን ባለፈ ለበርካቶች የሥራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ገልጸው፣ ከተማዋን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጥረት እያፋጠነ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.