የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ ለምክር ቤቱ ቀረበ

Jun 11, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2017(ኢዜአ)፦ የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።


ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 35ኛ መደበኛ ስብሰባ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ያቀረቡትን የፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ የበጀት መግለጫ አዳምጧል፡፡


የ2018 በጀት ዓመት የፌደራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና የፊሲካል ፖሊሲን ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡


ለ2018 በጀት ዓመት የተዘጋጀው ረቂቅ በጀት የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል የሆነውን የ2016-2018 የልማትና ኢንቨስትመንት እቅድ እና የፕሮግራም በጀት በማጣጣም የተቀመጡ ግቦችና አቅጣጫዎችን ከማስፈጸም አኳያ እና ሊኖር የሚችለውን የሀብት መጠን ከግምት በማስገባት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።


የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠል፣ የመንግስት ብድር ጤናማ እንዲሆን ከአበዳሪዎች ጋር የዕዳ ሽግሽግ ድርድር ማድረግ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሚያስከትለውን ጫና ለመቀነስ የማህበራዊ ወጪ ድጎማን ማስቀጠል በትኩረት ከሚሰሩት መካከል ጠቅሰዋል።


ከ2017 በጀት አንጻር የ34 ነጥብ 4 በመቶ እድገት እንዳለውም ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት፡፡


ወጪው የሚሸፈነው ከ80 በመቶ በላይ ከሀገር ውስጥ ገቢ ሲሆን አዳዲስ የታክስ ምንጮችን ወደ ገቢ ስርዓቱ በማስገባትና የነበሩትን በማጠናከር ገቢን ለመጨመር እንደሚሰራ አብራርተዋል።


በዚህም በ2018 በጀት አመት አጠቃላይ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱንም ተናግረዋል።


ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የተመደበላቸውን በጀት ለታለመለት አላማ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡


በመሆኑም የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።


ረቂቅ በጀቱ ለዝርዝር እይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.