የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የተገልጋዩን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ ነው

Jun 11, 2025

IDOPRESS

ባህርዳር፤ ሰኔ 3/2017 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን የተገልጋዩን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተመላከተ።

የባህር ዳር ከተማ በመንግስት አገልግሎትና ስታንዳርድ ሪፎርም አተገባበር ላይ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ አካሄዷል።


በንቅናቄ መድረኩ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት በክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን የሪፎርም ድጋፍና ክትትል ዳይሬክተር አቶ እንዳለው ይታይ እንደገለጹት በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ሰፊ ቅሬታ የሚያስነሳው ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ አለማድረግ ነው።

ችግሩን ለመቅረፍ እንደ ሀገር የወጣውን ፖሊሲ መሰረት በማድረግ አገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝ በማድረግ ተገልጋዩ ጊዜና ጉልበቱን ከመቆጠብ በተጨማሪ ፍትሃዊነቱ የተረጋገጠ አገልግሎት እንዲያገኝ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

ለመልካም አስተዳደር ችግሮችና ብልሹ አሰራሮች ምክንያት ከሆኑት አንዱ የሆነው ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን የመለየት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በዚህም እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም መጨረሻ ባለው ጊዜ የትምህርት ማስረጃ ለይቶ ለማጠናቀቅ ታስቦ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡ እውቀትንና ክህሎትን መሰረት ባደረገ አግባብ እንዲመራ ሲቪል ሰርቫንቱ እንደየ ዘርፉ የረጅም ጊዜና የስራ ላይ ስልጠና እንዲያገኝ የሚያስችሉ ተግባራትም እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የዘመነና የባህር ዳር ከተማን የሚመጥን የመንግስት አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን መተግበር ቀዳሚ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ ናቸው።

ከተማ አስተዳደሩ ከሚሰጠው ሰፊ አገልግሎት አንጻር የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት በኩል የሚነሱ ቅሬታዎችን መፍታት የሚቻለው በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ሲቻል መሆኑን አንስተው ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።


በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ እንደገለጹት የመንግስት አገልግሎትና ስታንዳርድ ሪፎርም ውጤታማ የሚሆነው በየደረጃው ያለ አመራር ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ሲችል ነው።

የንቅናቄ መድረኩ አላማም በየደረጃው ያለ አመራር ስለ ሪፎርሙ በአግባቡ ተገንዝቦ ለተግባራዊነቱ እንዲተጋ ማስቻል ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሲቪል ሰርቫንት እንዳለም መረጃዎች ያመላክታሉ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.