አዲስ አበባ፤ሰኔ 3/2017(ኢዜአ)፦ከአንበሳ ጋራዥ እስከ ጎሮ አደባባይ የተሰራው የኮሪደር ልማት የተሳለጠ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖርና በሰው እና ንብረት ላይ ይደርስ የነበረውን አደጋ ለመቀነስ ማገዙን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት አካል የሆነው የአንበሳ ጋራዥ፣ ጃክሮስ፣የጎሮ አደባባይ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወሳል፡፡
በልማቱ የመኪና፣የእግረኛና የብስክሌት መንገድ፣የህፃናት መጫወቻ፤ የመኪና ማቆሚያ፣ተርሚናሎች ፣መጸዳጃና ንግድ ቤቶች እንዲሁም መናፈሻዎች ተካተዋል፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪ ሻለቃ ሐይሉ ሎቤ እንዳሉት፤ የኮሪደር ልማቱ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ነው።
በአካባቢው ለበርካታ አመታት መኖራቸውን የተናገሩት ሻለቃ ሐይሉ ፤ መስመሩ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የሚታይበት ከመሆኑ ባለፈ በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ በርካታ አደጋዎች የሚከሰቱበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በተለይም በስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ከመገናኛ ጎሮ ለመድረስ አንድ ሰዓት ይፈጅ እንደነበር ገልጸው፤ ይህም ለስራ መስተጓጎል ምክንያት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱ የተሽከርካሪ፣ የብስክሌትና የእግረኛ መንገዶች ተለይተው በመሰራታቸው ይከሰት የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
አሽከርካሪ ኩምሳ አለሙ በበኩሉ፤የኮሪደር ልማቱ የአካባቢውን የትራፊክ እንቅስቃሴ ከማሳለጥ በዘለለ በየመንገዱ በመቆም ይባክን የነበረውን ጊዜ፣ ወጪና የነዳጅ ብክነት ያስቀረ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ግንባታው በአካባቢው ይከሰት የነበረውን የተሽከርካሪ አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ማስቻሉን በመጠቆም ሁላችንም በባለቤትነት ስሜት ልንከባከበው እና ልንጠብቀው ይገባል ነው ያለው፡፡
የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ መስፍን አበበ በበኩላቸው፥የኮሪደር ልማቱ በተለይ ለብስክሌት ተጠቃሚዎች ትልቅ እድል ይዞ የመጣ ነው ብለዋል፡፡
የመንገዱ መሰራት የትራፊክ መጨናነቅ ሳይገድባቸው ያለምንም መንገላታት በፈለጉት ሰዓት ወደ ፈለጉት አቅጣጫ እንዲንቀሳቀሱ እንዳስቻላቸው ነው የተናገሩት።
የኮሪደር ልማቱ አካባቢውን ያስዋበ እንዲሁም ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን ያሳለጠ ነው ያሉት ደግሞ አቶ አለማየሁ ተስፉ ናቸው፡፡
አቶ ገበየሁ መኮንን በበኩላቸው፥ ልማቱ የትራፊክ መጨናነቅን በማስቀረት ሁሉም ሰው በፈለገው ሰዓት ወደ ሚፈልገው ቦታ እንዲንቀሳቀስ አስችሎታል ብለዋል፡፡
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025