የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ በሰባት ከተሞች ከ115 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ ነው

Jun 11, 2025

IDOPRESS

ሆሳዕና ፤ ሰኔ 4/2017 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ሰባት ከተሞች ከ115 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ገለፀ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ከሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ በከተሞች እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ለሁሉም የተመቹ ከተሞችን የመፍጠር ዓላማን ይዞ እየተከናወነ መሆኑን ማንሳታቸው የሚዘነጋ አይደለም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸውም የኮሪደር ልማት ስራው ዘመናዊ ከተሞችን እውን ከማድረግ ባለፈ ዘመን ተሻጋሪ እሳቤን የያዘና በየጊዜው እየጨመረ ካለው የህዝብ ብዛት ጋር ተሰናስሎ እየተከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።

ከተማ ለዘርፈ ብዙ ተግባራትና ውጤቶች ሊገነባ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በዘለለ ለማህበራዊም ሆነ ሌሎች ችግሮች መፍትሄን ለመስጠት ከተሞችን የማዘመን ስራው አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎችም ህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ከማድረግ በተጨማሪ ከተሞችን ውብና ለነዋሪዎቻቸው የተመቹ እንዲሆኑ እያደረጉ መሆናቸው እየታየ ነው።


በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማና ኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በክልሉ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡

በዚህም በህብረተሰብ ተሳትፎና በመንግሥት ወጪ በሁለት ምዕራፍ 165 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ግንባታ ለማከናወን ታቅዶ በመጀመሪያው ምዕራፍ ከ115 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የኮሪደር ልማት እየተፋጠነ ይገኛል ብለዋል።

ይህም በክልሉ የክላስተር መቀመጫ በሆኑ ሰባት ዋና ዋና ከተሞች እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ልማቱ ከተሞችን ውብና ጽዱ በማድረግ ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።


የህብረተሰብ ተሳትፎ ለልማቱ መሳካት ከፍተኛ ድርሻ እንደሚወስድ የተናገሩት ኃላፊው በሀሳብ፣ በጉልበትና በገንዘብ እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ንብረቱን በማንሳት ጭምር ተሳትፎው የላቀ መሆኑን አንስተው በገንዘብ እስካሁን ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ተሳትፎ ማድረጉን አንስተዋል፡፡

በክልሉ በሁሉም ከተሞች አየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ በሚገኙ ተግባራት ሚናው የጎላ መሆኑን አቶ ስንታየሁ አክለዋል፡፡

ከከተሞቹም የሆሳዕና ከተማን የ24 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ግንባታ ስራ በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ሙሉ አገልግሎት እንደሚሰጥም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡


አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ደንበሎ አየለ እየተተገበረ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ከተማዋን ፅዱና ውብ ለነዋሪዎቿ ምቹና ተመራጭ እንድትሆን እንደሚያደርጋት ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የከተማው መንገዶች በእግር ለመንቀሳቀስ አዳጋች እንደነበሩ ጠቁመው የኮሪደር ልማት ስራው ይህንን ችግር መፍታቱንና ለነዋሪውም ምቹ አካባቢን የፈጠረ ነው ብለዋል።


የወልቂጤ ከተማ ነዋሪው ወጣት አቤል ማሞ በበኩሉ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ እየተካሄደባት የምትገኘው የወልቂጤ ከተማ የትራፊክ መጨናነቅ ያጋጥማት እንደነበር አስታውሷል።

በከተማው እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ግን የተጠቀሰውን ችግር ለመቅረፍ እንደሚያስችልና ከተማዋን ከሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋትም ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.