የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በኢትዮጵያ 23 ተቋማት 124 አገልግሎቶችን በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየሰጡ ነው - ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ(ዶ/ር)

Jun 20, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ 23 ተቋማት 124 አገልግሎቶችን በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመንና የመልካም አስተዳደር ቅሬታን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ሪፎርም እያከናወነች መሆኑም ኮሚሽነሩ ገለጸዋል።

ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ በትይዩ የምታስተናግዳቸውን 10ኛው የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት የመንግሥት አገልግሎት አስተዳደር እና የተመድ የአፍሪካ ቀጣናዊ ፎረም በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ጉባኤዎቹ ከሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ አፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ እንደሚካሄዱ አስታውቀዋል።

የአፍሪካ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ጉባኤ በየሁለት ዓመቱ የሚከናወን አህጉራዊ ኹነት መሆኑ ተመላክቷል።

ጉባኤው የመንግሥት ተቋማት ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ተቋቁመው በየዘመኑ እየተንከባለሉ የመጡ ፈተናዎችን በፍጥነት ለመፍታት እንዲችሉ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

"የመንግሥት አገልግሎት እና ኢኖቬሽን" በሚል መሪ ሀሳብ በትይዩ የሚከናወነው የተመድ የአፍሪካ ቀጣናዊ ፎረም ፈጠራ በታከለበት መንገድ ሰው ተኮር አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የ2030 የተመድ 17 ዘላቂ የልማት ግቦችና የአፍሪካ ሕብረት የ2063 አጀንዳ 20 ስትራቴጂያዊ ግቦችን ለማሳካት ጠንካራ ተቋም የመፍጠር ዓላማ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የተመድ ዘላቂ የልማትና የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ላይ የተቀመጡትን ግቦችን ለማሳካት የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም በመቀየስ የፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፍ አዘጋጅታለች ብለዋል።

በተለይም የመንግስትን አገልግሎት ቀልጣፋና ግልጽ ማድረግ የሚያስችል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመጀመር ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በአንድ መሶብ አገልግሎት 23 ተቋማት 124 አገልግሎቶችን እየሰጡ መሆኑን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ሁሉም ክልሎች ቢያንስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲኖራቸው ይደረጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪሮርም እና በአንድ መሶብ አገልግሎት ምክንያት እነዚህን ሁለት አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ኹነቶች በትይዩ እንድታዘጋጅ መመረጧን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን በሶስት ምዕራፎች በማከናወን በመጀመሪያው ስምንት በሁለተኛው ዘጠኝ እንዲሁም በሶስተኛው ሰባት ተቋማት ላይ ሪፎርሙ ተፈፃሚ ይሆናል ብለዋል።

በሁሉም ምዕራፎች የዝግጅት፣ የተግበራና የማጽናት ምዕራፎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በመጀመሪያው የሪፎርም ሙከራ ትግበራ ወደ ተግባር ምዕራፍ እየገቡ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርሙ የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን ላይ ትኩረት ማድረጉንም ኮሚሽነሩ ጨምረው ተናግረዋል።

የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ሥራን ቆጥሮ የሚያስረክብና የሚረከብ ጠንካራ አመራር ለመፍጠር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመንና የመልካም አስተዳደር ቅሬታን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ሪፎርም እያከናወነች መሆኑንም ገለጸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.