የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ በሚቀጥሉት 90 ቀናት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያሳድጉ ተግባራት ይከናወናሉ

Jun 20, 2025

IDOPRESS

ወላይታ ሶዶ፤ ሰኔ 12/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚቀጥሉት 90 ቀናት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያሳድጉ ተግባራት በተቀናጀ መንገድ እንደሚከናወኑ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተናገሩ።

በመጀመሪያ ዙር የ90 ቀናት ዕቅድ አፈጻጸም ላይ የታዩ ክፍተቶችን በማረም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መወሰናቸውንም ከፍተኛ አመራሮቹ ገልጸዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ(ዶ/ር)፤ በሚቀጥሉት 90 ቀናት የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ይከናወናሉ።

የመኸር እርሻ ስራን ጨምሮ ያሉትን አቅሞች በአግባቡ ለመጠቀም በተቀናጀ መንገድ እንደሚሰራ ጠቅሰው ተግባራቱን በተሻለ ውጤታማ የሚያደርግ ዕቅድ ተዘጋጅቶ እስከታች ድረስ መውረዱን ገልጸዋል።

ባለፉት 90 ቀናትም 844ሺህ ሄክታር ማሳ በበልግ አዝመራ መልማቱንና 119ሺህ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችም ሲተከሉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ ንጋቱ ዳንሳ፣ በክልሉ ባለፉት 90 ቀናት ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

የሌማት ትሩፋትን በማሳለጥ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰራው ስራ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር ሂደትም ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይ 90 ቀናትም የተለጠጠ ዕቅድ በማዘጋጀት ለመፈጸም ከፍተኛ ርብርብ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

በክልሉ የወላይታ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ ዘውዱ ሳሙኤል በበኩላቸው ባለፉት 90 ቀናት የጋራ ትርክት ለማስረጽ የተሰራው ስራ ውጤት አሳይቷል ብለዋል።

በተለይም የአደጋ ስጋትን በራስ አቅም መቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው ይህን ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የከተማ ኮሪደር ልማት ደግሞ ከተሞችን ውብና ጽዱ በማድረግ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ያለ በመሆኑ ወደ ተለያዩ ከተሞች እያሰፋን እንገኛለን ብለዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር)፤ ባለፉት 90 ቀናት የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ 31ሺህ ቶን ቡና ለመሰብሰብ ታቅዶ 32ሺህ 500 በላይ ቶን ቡና በመሰብሰብ ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።

የህዝቡን ሰላም በማስጠበቅ ዞኑን የፍቅር እና የአንድነት ማዕከል ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 2ኛ ዙር የ90 ቀናት ዕቅድ "ለጥጦ ማቀድ አልቆ መፈጸም'' በሚል መሪ ሃሳብ ከሰኔ 5 እስከ ጳጉሜ 5/ 2017 ዓ. ም ድረስ የሚተገበር መሆኑን ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.