አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2017(ኢዜአ)፦ የፍጆታ እቃዎች ድጎማን ከማህበረሰቡ ፍላጎትና አቅርቦት ጋር በማጣጣም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 38ኛ መደበኛ ስብሰባ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የ11 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ተወያይቷል።
የምክር ቤቱ አባላት የጥራጥሬ ምርቶች የወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን፣ የፍጆታ እቃዎች በተለይም ከዘይትና ስኳር ስርጭት ድጎማ ጋር የተያያዙ ችግሮችን አንስተዋል።
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችና የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከላት ተደራሽነት፣ እንዲሁም የጠረፍ ንግድ ስምምነቶች ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባም ገልጸዋል።
እንዲሁም የነዳጅ ማደያዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ተደራሽ አለመሆንና ህገ-ወጥ የነዳጅ ስርጭትና ግብይትን አስመልክተው ጥያቄ አንስተዋል፡፡
የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አመርቂ ውጤቶች ቢመዘገቡም የንግድ ፍቃድን ለመመለስ የሚታየው የቢሮክራሲ ችግር መፈታት ይኖርበታል ብለዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) እንደተናገሩት አንዳንድ የጥራጥሬ ምርቶች ላይ ዝቅተኛ አፈጻጻም የተገኘው በአለም አቀፍ ዋጋ መቀነስና የአንዳንድ ገዢ ሀገራት ፍላጎት በመቀዛቀዙ ሳቢያ ነው።
የጠረፍ ንግድ ላይ ህገ-ወጥ ንግድ በወጪ ንግድ ላይ ተጽዕኖ እንዳያደርስ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የነዳጅ ስርጭትና ግብይትን በተመለከተ ተጨማሪ የነዳጅ ማደያዎች የሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎችን ለመለየት ጥናት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የንግድ ምዝገባና ፍቃድ ለመመለስ ከግብር ጋር በተያያዘ የማጣራት ስራዎች ጊዜ የሚፈጁ መሆናቸውን ጠቁመው ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ችግሩን ለመፍታት እንሰራለን ብለዋል።
በመላ ሀገሪቱ በ11 ወራት በተደረገ ክትትል ከ269ሺህ በላይ ድርጅቶች ላይ የህግ መተላለፍ ችግር በመገኘቱ አርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል።
በድጎማ የሚገቡ የፍጆታ እቃዎች ላይ የሚታየውን የስርጭት ችግር ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተጨማሪ ግዢ ለመፈጸም እየሰራን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከላት በሁሉም አርብቶ አደሮች አካባቢ ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አይሻ ያህያ ከ500 ወረዳዎች በላይ የነዳጅ ማደያዎች አለመኖሩን ጠቅሰው፤ ለእነዚህ አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በየአካባቢዎቹ የነዳጅ ማደያዎችን ገንብተው ወደ ስራ ለመግባት የሚኒስቴሩን ፍቃድ ለሚፈልጉ ባለሀብቶችም ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የፍጆታ እቃዎች ድጎማ በተለይም ዘይትና ስኳር ከማህበረሰቡ ፍላጎትና አቅርቦት ጋር በማጣጣም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶችን የሚያመርቱና ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡ ተቋማት ላይ ጠንካራ ህጋዊ እርምጃ መወሰድ አለበትም ነው ያሉት።
በወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ትልቅ ሰኬት መሆኑን ገልጸው፤ ሀገሪቱ ካላት እምቅ አቅም አንጻር ገቢው እንዲጨምር የሚከናወኑ ስራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025