የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በህገ-ወጥ ነዳጅ ማደያዎች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)

Jun 23, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2017(ኢዜአ)፦ በህገ-ወጥ ነዳጅ ማደያዎች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ከነዳጅ ግብይት ጋር ተያይዞ በነዳጅ ማደያዎች የተስተዋለውን ሰልፍ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም መንግስት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የነዳጅ ዋጋን ከአለም ዋጋ ጋር የማጣጣም ስራ መስራቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በየወሩ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እንደማይኖር ጠቁመው፤ የነዳጅ ዋጋ በአለም አቀፍ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ይወሰናል ብለዋል፡፡

አንዳንድ ነዳጅ ማደያዎች የዋጋ ማሻሻያ ይኖራል ብለው በማሰብ ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር አድርገዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ በመግለጫቸው።

በአዲስ አበባ ምንም አይነት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪም ሆነ የአቅርቦት እጥረት አለመኖሩን በክትትል ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በተደረገው ክትትል አዲስ አበባ ውስጥ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሊትር ነጭ ናፍጣ እና 3 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን መኖሩን ማረጋገጥ መቻሉን አመላክተዋል፡፡

በድምሩ 5 ነጥብ 3 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ እያለ ነው በህገ ወጦች የነዳጅ እጥረት እንዳለ ለማስመሰል ሙከራ የተደረገው ብለዋል፡፡

ይህ በአቋራጭ ለመክበርና የራስ ያልሆነን ገንዘብ ለማጋበስ የሚደረግ ጥረት መሆኑን አመልክተው በዚህ ህገ-ወጥ ስራ ላይ ተሰማርተው የተገኙ ሁለት የነዳጅ ማደያዎች ሙሉ ለሙሉ ከግብይት ስርዓቱ እንዲወጡ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በህገ-ወጥ ነዳጅ ማደያዎች ላይ የሚወሰደው መሰል ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ሚኒስትሩ ያስታወቁት፡፡

መንግስት ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ እያወጣ የነዳጅ ምርት እያቀረበ እንደሚገኝ አመላክተው የምርት እጥረት ሳይኖር እንዳለ የሚያስመስሉ ህገ-ወጦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡

በንግድ አዋጁ መሰረት ምርቶችን የመደበቅ ወንጀል ከ300 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እና የማደያ ባለቤቱን ከ2 እስከ 5 ዓመት እስራት የሚደርስ የእስር ቅጣት እንደሚያስቀጣ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.