
አዲስ አበባ፤ሰኔ 23/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ስትራቴጂ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻነቷን የሚያጠናክር መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ገለጹ።
ለአምስት ዓመታት የሚተገበረው ይህ ስትራቴጂ ከሐምሌ1/2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በስትራቴጂው ዙሪያ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የልማት አጋሮችና የግሉ ዘርፍ በተሳተፉበት ተካሂዷል።

ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የሕግና ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ጨምሮ በርካታ የለውጥ ተግባራት ተከናውነዋል።
ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ የኢኮኖሚ መስኮች ከለውጡ ወዲህ ለኢንቨስትመንት ክፍት መደረጋቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህን ለውጦች ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል የኢንቨስትመንት መሳቢያ ስትራቴጂ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
በአዲስ መልክ የተዘጋጀውና የኢትዮጵያን እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም ለማስተዋወቅ የሚረዳው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ስትራቴጂ አዳዲስ የተከፈቱ የኢንቨስትመንት መስኮችን አካትቶ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
ስትራቴጂው የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅም በማስተዋወቅ ሂደት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ከማስቻሉም በላይ ለባለሃብቶች ወጥ የሆነ የኢንቨስትመንት መረጃ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
ስትራቴጂውን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የድርጊት መርሃ ግብር እንደሚዘጋጅ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያን በአፍሪካም በዓለምም ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የተያዘው ሀገራዊ ግብ እንዲሳካ ስትራቴጂው ጉልህ ሚና እንደሚጫወትም ጠቁመዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው፤ ለውጡን ተከትሎ የተሻሻለው አዲሱ የኢንቨስትመንት አዋጅ የቱሪዝም ልማትን የሚያሳልጡ አሰራሮች መያዙን ጠቅሰዋል።
በቱሪዝም ዘርፍ ለኢንቨስትመንት የሚሆኑ አካባቢዎችን የመለየት ሥራ መከናወኑን የገለጹት ሚኒስትር ደኤታው፤ በመስኩ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የስትራቴጂው እውን መሆን ወቅታዊ እና ትልቅ ውጤት የሚያመጣ ነው ብለዋል።
ከምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሞሃን ፒ ኤል ሲ ሥራ አስኪያጅ ሀርሽ ኩታሪ እንዳሉት፤ ስትራቴጂው የውጭ ባለሃብቶችን ተሳትፎ የሚያሳድግ በመሆኑ ትልቅ እርምጃ ነው።

አንድ ኢንቨስትመንት ከመነሻው ጀምሮ አጠቃላይ ሂደቱን በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ መከታተል የሚያስችል አሰራር በስትራቴጂው መካተቱም የኢንቨስትመንት ውጤታማነትን በእጅጉ የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
የዞስካለስ ፓርትነርስ ኩባንያ ተወካይ እሴት ልዑልሰገድ በበኩላቸው፤ ኢንቨስትመንት የመሳብ ጥረት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን አገልግሎት አሰጣጡን የበለጠ ለማሻሻል መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተከናወኑ ተግባራትን በተሻለ መልኩ ማስተዋወቅ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ስትራቴጂ እ.ኤ.አ. ከ2025 እስከ 2030 ድረስ የሚተገበር ሲሆን፥ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በተሻለ መልኩ ለመሳብ የሚያስችል መሆኑም ተመላክቷል።
ጅግጅጋ፤ ሚያዝያ 13/2018 (ኢዜአ)፦ በኦዲት ዘርፍ በተከናወኑ የሪፎርም ተግባራት ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ...
Apr 22, 2026
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 7/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በምግብ ዋስትና እና በኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት ለመላው አፍሪካ አገራት ትልቅ አ...
Apr 16, 2026
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ለውጡ የሀገሪቱን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶች በመጠገን፣ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ከፍታና ለማህበራዊ ትስስ...
Apr 3, 2026
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025