አዲስ አበባ፤ሰኔ 25/2017(ኢዜአ):-በቦረና ዞን እየተከናወኑ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ስራዎች የአርሶና አርብቶ አደሩን ህይወት በተጨባጭ በመቀየር ላይ መሆናቸውን በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ ገለጹ።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በቦረና ዞን እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱም በክላስተር እየለማ የሚገኝ የስንዴ ክላስተር፣ የቀበሌ አስተዳደር የስራ እንቅስቃሴ፣ የቦረና ከብቶች ማድለቢያ ቦታን ጨምሮ በግንባታ ላይ የሚገኘውን የቦረና ባህል ማዕከልን ጎብኝተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ ጉብኝቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ በቦረና ዞን እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ህይወት በተጨባጭ እየቀየሩ ይገኛሉ ብለዋል።
በክላስተር እየለማ የሚገኘው የስንዴ ምርትም አካባቢው ላይ የስንዴ ምርታማነት እያደገ ለመሆኑ ማሣያ ነው ብለዋል።
ዞኑ ከዚህ ቀደም ተከሰቶ ከነበረው ድርቅ በማገገም ምርታማነትን በተጨባጭ እያረጋገጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በኦሮሚያ ክልል በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የቀበሌ አስተዳደር መዋቅር ህዝቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በቦረና ዞን ደረጃቸውን የጠበቁ የቀበሌ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች ወደ ስራ የገቡ ሲሆን፥ የአርብቶ አደሩን እንግልት በመቀነስ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በፍጥነት እንዲቀረፉ ማስቻሉን ጠቁመዋል።
የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱልሰላም ዋሪዮ በበኩላቸው፥ በዞኑ ከሁለት ወራት በፊት በተጀመረው የክረምት ወራት የግብርና ልማት 135 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ የዘር ዓይነቶች መሸፈኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥም ከ56 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በክላስተር እየለማ መሆኑን ጠቅሰው፥ 5 ሺህ ሄክታር በስንዴ ምርት የተሸፈነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ስንዴ፣ ቦሎቄ፣ ጤፍ፣ ማሾ እና ሌሎችም ሰብሎችን ማልማት መቻሉን በመግለፅ፥ ከዚህም 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የቦረና ዞን አሁን ላይ በተሻለ ምርታማነት ላይ እንደሚገኝ አስረድተው፥ የአርብቶ አደሩ የስራ ባህል እየተቀየረ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቦረና ዞን የድሬ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ጃተኒ ቦሩ እና አብዱላሂ ቆዳ ስንዴን በክላስተር በማልማት ምርታማ በመሆን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በመንግሥት በኩል ምርጥ ዘርን ጨምሮ የተለያዩ ግብዓት እየቀረበላቸው በመሆኑ ምርታማነትን እያሳደገልን ነው ብለዋል።
በዱቡሉቅ ወረዳ አኖሌ ቀበሌ ነዋሪዎች ኖሌ ኮርማ እና ሮባ ጎዳና የቀበሌ አስተዳደር ከመኖሪያቸው በአቅራቢያ መቋቋሙ እንግልትን እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025