የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የአደባባይ በዓላት የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በማስፋፋት ለዘርፉ እድገት ገንቢ ሚና አላቸው - ቱሪዝም ሚኒስቴር 

Oct 14, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በማስፋፋት ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ መንግስት ቱሪዝምን እንደ ትልቅ የኢኮኖሚ መስክ በመውሰድ ዘርፉን የሚያነቃቁ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን፣ ታሪካዊ ቅርሶችን እንዲሁም የማይዳሰሱ ትውፊቶችን በአግባቡ ለመጠቀምና በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በከፍተኛ ደረጃ መሰራቱ አንስተዋል።

በመዲናዋ ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ማስፋት መቻሉ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቁጥር በመጨመር ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲያድግ ማስቻሉንም ተናግረዋል፡፡

በመላው ሀገሪቱ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት የሀገር ገፅታ በመገንባት ረገድ አቅም እየፈጠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በተለይም በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለሀገር ውስጥ የቱሪዝም እድገት ፋይዳቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ቅርሶቹ ከውጪ ጎብኚዎች ከሚገኘው ገቢ በላይ በዩኔስኮ በኩል ለጥናትና ምርምር የሚመጡት ሃብቶች በርካታ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ትርክቶችን ለዓለም በማስተዋወቅ አትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአፍሪካ ያላትን ቦታ በማጉላት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የአደባባይ በዓላቱ ሲከበሩ የሀገር ባህል ልብስ በስፋት የሚፈለግበት ወቅት መሆኑን ጠቅሰው፤ የስራ እድል ከመፍጠር አኳያም ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል።

በቱሪዝም መዳረሻዎች አስፈላጊው መሰረት ልማት እንዲሟላ መደረጉ ለጎብኚዎች እርካታ ከመፍጠር ባለፈ ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ እያደረገ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡

በተለይም በመዲናዋ የተሰሩ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች፣ መሰረተ ልማቶች እንዲሁም የኮሪደር ልማት ስራዎች ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እያስገኙ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ የበዓላቱ ልዩ ድምቀት የሰጠ እና የበዓሉ ታዳሚዎች ያለ ምንም መገፋፋት በነፃነት እንዲያከብሩ ማስቻሉንም ጠቁመዋል።

በዚህም የኮሪደር ልማት ለቱሪዝም እድገት የመጣ ሲሳይ ነው ብለን መግለፅ እንችላለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.