የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ያጣችው መጭውን ትውልድ ባላገናዘበው የወቅቱ አሥተዳደር ቸልተኝነትና ሰው ሠራሽ ሴራ ነው-ምሁራን

Oct 17, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ያጣችው መጭውን ትውልድ ባላገናዘበው የወቅቱ አሥተዳደር ቸልተኝነትና ሰው ሠራሽ ሴራ መሆኑን የፖለቲካል ሳይንስ መምህራን እና የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተመራማሪዎች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት ሁኔታ እንደሚያስቆጭም ምሁራኑ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

ከሀገራዊ ብሎም ቀጣናዊ ትብብርን ማጎልበት እና ትስስርን ከማደርጀት አኳያ የባሕር በር ለማግኘት የሚደረግ ጥረት የአንድ ፓርቲ እና መንግሥት ፍላጎት ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበትም አስገንዝበዋል።

የባሕር በር የነበራት ኢትዮጵያ፤በሯን ተፈጥሯዊም ሆነ ሕጋዊ መሠረት በሌለው ሁኔታ በወቅቱ የአሥተዳደር ድክመት ምክንያት ማጣቷን በዲላ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር፣ የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተመራማሪ እና ደራሲ ዳዊት መዝገበ አውስተዋል።

የባሕር በር ማግኘት ማለት ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳው እና ሌሎችም ጥቅሞቹ የጎሉ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል።

ለሕዝቦች ትስስር፣ለቀጣናዊ ትብብር እና በጋራ ለመልማት የባሕር በር ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉዓለም ኃይለማርያም በበኩላቸው፥ዘርፈ-ብዙ ጥቅም ያለውን የባሕር በር ለማግኘት ኢትዮጵያ ያነሳችው ጥያቄ ሕዝባዊ ድጋፍ እንዳለው ጠቅሰው ተገቢነቱንም አንስተዋል።

ከብሔራዊ ጥቅም አጀንዳዎች መካከል አንዱ መሆኑን አንስተው፥የጥያቄውን መነሳት በበጎ የወሰዱ ሀገራት መኖራቸውንም ተናግረዋል።

መንግሥት እየሄደበት ያለውን ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ አድንቀው፤የባሕር በር ለማግኘት አዋጭ የሆኑ የተለያዩ አማራጮችን መከተል መልካም ስለመሆኑ መክረዋል።

ኢትዮጵያን ያህል ታሪካዊ፣ትልቅ እና በርካታ ሕዝብ የሚኖርባት ሀገር የባሕር በር እንዳይኖራት የሚያደርጉ ሂደቶች ሕጋዊም ሆነ ፖለቲካዊ ቅቡልነት እንደሌላቸውም ነው ምሁራኑ ያነሱት።

ጥረቶችን አጠናክሮ መቀጠል እና ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን፣ በዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጭምር ግንኙነትን ማጥበቅ ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት እንዳለባት በማመን ጥረቶችን መጀመሯ ተገቢ መሆኑን ጠቁመው፤እንዴት ባለ መንገድ ማግኘት እና መጠቀም ይቻላል የሚሉት ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

የባሕር በር ጥያቄ ሲንከባለል መቆየቱንና በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ መኖሩን እንዳስተዋሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.