🔇Unmute
አዶላ ፤ ጥቅምት 18/2018 (ኢዜአ)፡- በታማኝነት ግብር በመክፈላችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚፈቱ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ሲሉ የጉጂ ዞን የአዶላ ከተማ ግብር ከፋዮች ገለጹ።
በተያዘው በጀት አመት በዞኑ ሁሉንም የገቢ አቅሞች በመጠቀም ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱ ተመልክቷል፡፡
በዞኑ አዶላ ከተማ የነዳጅ ምርቶች አቅራቢና አከፋፋይ የሆኑት አቶ ባሳዬ ሀይሉ፣ ግብርን በታማኝነት መክፈል ለሀገር ልማት መሰረት መሆኑን በመገንዘብ ገቢያቸውን በወቅቱ በማሳወቅ ግብር እየከፈሉ እንደሆነ ተናግረዋል።
ግብር መክፈል ተመልሶ ለራስ ጥቅም የሚውል በመሆኑ በታማኝነት ግብራቸውን ከመክፈል አልፈው ሌሎችም ለዚህ ጉዳይ እንዲተባበሩ ምክር እየለገሱ መሆኑን ገልጸዋል።
ገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤትም የግብር ከፋዩን ግዜ የሚቆጥቡ አሰራርን በመዘርጋቱ ከስራቸው ሳይነጠሉ ግብር መክፈላቸውን ጠቅሰዋል።
ግብር በወቅቱ መክፈል የዜግነት ግዴታ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚፈቱ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚከናወንበት መሆኑን በመረዳት ግብር በወቅቱ እየከፈሉ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ በከተማው በተለያዩ የንግድ ስራዎች የተሰማሩት አቶ ዮሀንስ አብዲ ናቸው።
ከንግድ ስራቸው የሚያገኙትን ገቢ በማሳወቅ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው ግብራቸውን በመክፈል ድካምና ጊዜያቸውን መቆጠብ እንደቻሉ ገልጸዋል።
የልማትና የአገልግሎት ጥያቄዎችን ለማቅረብ ግብርን በታማኝነት መክፍል ከሁሉም አገር ወዳድ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው በሆቴል ስራ የሚተዳደሩት አቶ ፍቃዱ ግዛው በበኩላቸው በራስ አቅም የተገነቡ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ግብር በታማኝነትና በወቅቱ የመክፈል ውጤቶች ናቸው ብለዋል።
የጤና፣ የትምህርት፣ የመጠጥ ውኃ፣ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ሊሰሩ የሚችሉት በሀገር ውስጥ ከሚሰበሰብ ገቢ መሆኑን በመገንዘብ ግብርን በታማኝነት መክፈላቸውን ጠቁመዋል።
የጉጂ ዞን ገቢዎች ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ እሸቴ ታሪኩ፣ በዞኑ የግብር አሰባሰብ ስርአቱን ለማዘመን የዲጂታል ቴክኖሎጂ አማራጭን በመዘርጋት የንግዱን ማህበረሰብ ጊዜን መቆጠብ እንዳስቻለ ገልጸዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመትም 3 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አስታውሰው ባለፉት ሶስት ወራት 954 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ ከ157 ሚሊዮን ብር በላይ ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትና ከልዩ የገቢ ምንጮች የተሰበሰበ መሆኑን ገልጸዋል።
የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው በጀት አመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር 507 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ግብር ከፋዩ ካለበት ሆኖ ግብርን በዲጂታል አማራጭ የሚከፍልበት ስርአት መዘርጋቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰው በሶስት ወራቱ 375 አዳዲስ ነጋዴዎች ወደ ታክስ ስርአቱ እንዲካተቱ መደረጉንም አክለዋል።
በጉጂ ዞን ከ11 ሺህ በላይ ቋሚና መደበኛ ግብር ከፋዮች እንዳሉ ተመልክቷል።
ቦንጋ ፤የካቲት 16/2017 (ኢዜአ) ፡-በቦንጋ ከተማ የተካሄደውን የህዝብ ውይይት የመሩ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በከተማው የተለያዩ የልማት ...
Feb 24, 2025
ደብረብርሀን፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የገበያ ማዕከላት ግንባታ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አምስት አመታት በወረቀት የሚካሔዱ አሰራሮችን በማስቀረት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና አገልግሎት በተሻለ ...
Feb 8, 2025