የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በደብረ ብርሃን ከተማ ከ150 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ አምራች ኢንዱስትሪዎች  ወደ ስራ ገብተዋል 

Nov 13, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2018(ኢዜአ)፦ በደብረ ብርሃን ከተማ ከ 150 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ መግባታቸውን የከተማዋ ከንቲባ በድሉ ውብሸት ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ የተገነባውን ብራውን ፉድ የበቆሎ፣ ብቅልና አልሚ ምግብ ማምረቻ ፋብሪካ መርቀዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ ከንቲባ በድሉ ውብሸት በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የለውጡ መንግስት ለልማት በሰጠው ትኩረት በኢንዱስትሪና ከተማ ልማት እመርታዊ ስኬት ተመዝግቧል፡፡

የደብረብርሃን ከተማ በኢትዮጵያ የተመዘገበው ለውጥ ተቋዳሽ መሆኗን በማንሳት፤ ባለፉት ዓመታት ከ150 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ወደ ስራ የገቡ አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ከ30 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸው፤ ወደ ሙሉ ማምረት ሲሸጋገሩ አሃዙ ወደ 150 ሺህ ከፍ ይላል ብለዋል፡፡

ከተማዋ ለአዲስ አበባ ያላት ቅርበት፣ ኢንዱስትሪን እንደ ዐይኑ ብሌን የሚመለከት ሰላም ወዳድ ማህበረሰብ መኖሩና የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻሉ ለኢንዱስትሪው መስፋፋት ገንቢ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡

ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ፣ የኮሪደር ልማት እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መከናወናቸውን በመጥቀስ፤ የመንግስትን አገልግሎት ለማሳለጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች የመኖሪያ ቦታ ማግኘታቸውን ገልጸው፤ በ2018 በጀት ዓመት 10 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

የብራውን ፉድ ፋብሪካ የበቆሎ ምርትን በመጠቀም በቫይታሚን የበለጸጉ የምግብ ምርቶች እና የእንስሳት መኖ በማምረት የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

የብራውን ፉድ ፋብሪካ ባለቤት ብሩክ ወርቁ ፋብሪካው የበቆሎ ምርትን በግብዓትነት የሚጠቀም መሆኑን በመግለጽ፤ ገቢ ምርትን ማስቀረት ያስችላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የበቆሎ ምርትን በመጠቀም በቫይታሚን የበለጸገ አልሚ ምግቦችን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ጥራትና ብዛት ለገበያ ለማቅረብ እንደሚያስችላቸውም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.