የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የጣናነሽ ቁጥር -ሁለት ጀልባ ሥራ መጀመር የቱሪዝም ዘርፉን እያነቃቃው ነው - አስጎብኚዎች  

Nov 13, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

ባሕር ዳር ፤ ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፦የጣናነሽ ቁጥር - ሁለት ጀልባ ሥራ መጀመር በጣና ሐይቅ ሲሰጥ የቆየውን የትራንስፖርት አገልግሎት ይበልጥ በማዘመን የቱሪዝም ዘርፉን እያነቃቃ መምጣቱን በባሕር ዳር ከተማ አስጎብኚዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በባሕር ዳር ከተማ ተገኝተው ጣናነሽ ቁጥር-2 ጀልባን ሥራ በይፋ ማስጀመራቸው የሚታወስ ነው።

የጀልባዋን ሥራ መጀመር በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ከተማ አስጎብኚዎች እንዳሉት፤ የጀልባዋ ወደሥራ መግባት በጣና ሐይቅ ላይ የነበረን ዘመኑን የማይመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት ቀይሮታል።

አገልግሎቱን በማዘመን ዘርፉን እያነቃቃው መምጣቱንም ነው የተናገሩት።


ከአስጎብኚዎቹ መካከል አቶ አበበ ያረጋል፤ የጀልባዋን ሥራ መጀመር በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማራው ማህበረሰብ በጉጉት ሲጠብቀው እንደቆየ ተናግረዋል።

ለቱሪስቶች በጣና ሐይቅ ላይ የሚገኙ ታሪካዊና ባሕላዊ የመስህብ ሃብቶችን ለመጎብኘት ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱንም ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በጣና ሐይቅ ዘመኑን በማይዋጅ፣ ምቾትና ፍጥነት በሌላቸው አነስተኛና ያረጁ ጀልባዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አዲሷ ጀልባ ፈጣን፣ ዘመናዊና ምቾት ያላት በመሆኗ በርካታ ጎብኚዎች ጀልባዋን ለመጠቀም ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሌላው በአስጎብኚነት ሥራ የተሰማሩት አቶ አበባው ሲሳይ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም በርካታ ጎብኚዎች በአንድ ጊዜ ሲመጡ ለማስተናገድ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

የነበሩ ጀልባዎች አነስተኛና ውስን ሰው ብቻ እንደሚይዙ ጠቁመው፤ ጣናነሽ ቁጥር-ሁለት ጀልባ ብዛት ያለው ሰው የመያዝ አቅም ስላላት ችግሩ መፈታቱን ተናግረዋል።


ጀልባዋ ለጉዞ የሚያስፈልጉ ግብአቶች የተሟላላት በመሆኑ የጎብኚዎችን ቀልብ የመሳብ አቅሟም ከፍተኛ ነው ብለዋል።

አቶ ኤፍሬም አብርሀም የተባሉ ሌላው አስጎብኚ፤ የጀልባዋ ስራ መጀመር በጣና ሐይቅ ለሚከናወነው የቱሪዝም ሥራ አዲስ መነቃቃት እየፈጠረ መምጣቱን ተናግረዋል።

ሐይቁ የታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ መስህብ ሃብት መገኛ በመሆኑ ይህን ዘርፍ ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማዋል የጀልባዋ ሥራ መጀመር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ አፋር ክልልና አዲስ አበባ አድርጋ ጠመዝማዛና አስቸጋሪውን የዓባይ በረሃን መንገድ በማቋረጥ ባሕር ዳር ከተማ የደረሰችው ጣናነሽ ቁጥር- ሁለት ጀልባ በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ አገልግሎት ድርጅት የተገዛች ናት።

ቀደም ሲል አገልግሎት ሲሰጡ ከቆዩት ጀልባዎች በዘመናዊነቷ ፣ በተገጠመላት ቴክኖሎጂ ፣ በፍጥነቷና ለጎብኚዎች ባላት ምቾት ለየት ያለች እንደሆነ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.