የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ያስገኛል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

Nov 20, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ፤ሕዳር 7/2018 (ኢዜአ)፡- ብልሹ አገልግሎት አሰጣጥን በማስወገድ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ረገድ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሚና የጎላ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደሴ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።


በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር በተለያዩ መድረኮች ሕዝቡ ካነሳቸው ጉዳዮች አንዱ የአገልግሎት አሰጣጣችሁን ፈትሹ፤ ከእጅ መንሻ ነጻ የሆነ አገልግሎት ልናገኝ ይገባል የሚል ነበር ሲሉ አውስተዋል።

በዚህም መሠረት በተቋማት የሚስተዋሉ ብልሹ አገልግሎት አሰጣጦችን በማስወገድ ዘመኑን የዋጀና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ወደ ሥራ እያስገባን ነው ብለዋል።

አስተዋዩ የደሴ ሕዝብ ልማት ፈላጊ፣ ለፍትሕ የቆመ፣ በውይይት የሚያምን፣ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራና የጸና መሆኑንም በንግግራቸው አንስተዋል።

ደሴ ከተማ በከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ እንደምትገኝ ተመልክተናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን የልማት ጉዞ በማሳለጥ ረገድ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት የጎላ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።


መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተለያዩ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት፣ ከዚህ በፊት በማንዋል ይሰጥ የነበረውን የመንግሥት አገልግሎት በዲጂታል ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን እንግልት የሚቀንስ መሆኑንም አስረድተዋል።

ተገልጋዮች ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸው ብሎም ጉልበታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማድረግ ረገድ መሶብ የአንድ ማዕከል ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከሲቪል ሰርቪስ ማሻሻ ሪፎርሞች ውስጥ አንዱ አካል እንደሆነ ገልጸው፤ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሳድግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በይበልጥ ማስፋፋትና ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።


በሌላ በኩል የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ወደ ሁሉም አካባቢዎች መድረስ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ጽዳትና ውበት የደሴ መገለጫዎች ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህ ደግሞ የከተማዋ ነዋሪዎች በተለይም የንግዱ ማኅበረሰብ ግብሩን በወቅቱና በታማኝነት መክፈልና ተጨማሪ አስተዋጽኦም በግሉ ማበርከት እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል።

የኮሪደር ልማትና የኢትዮጵያን ብልጽግና በሚፈለገው ልክ ለማሳካት እያንዳንዱ ማኅበረሰብ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ሰላምና ልማት ተመጋጋቢ በመሆናቸው ሕዝቡ ሰላሙን ማስጠበቅ እንዳለበትም በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.