🔇Unmute
ጅማ ፤ ግንቦት 29/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው ዓመት 370 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቡና ችግኝ እንደሚተከል የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በጅማ ዞን ማና ወረዳም የዘንድሮው የቡና ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በይፋ ተጀምሯል።
በስፍራው ተገኝተው መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ፤ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰራው ስራ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘንድሮ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን የቡና ችግኞች ተዘጋጅተው በ370 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየተተከሉ መሆኑን እና ይህም የክልሉን አጠቃላይ የቡና ምርት ሽፋን ወደ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ከፍ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
በቀጣይም ምርታማነቱን ይበልጥ ለማሳደግ ከግብርና ምርምር ማዕከላት ጋር በመተባበር የተሻሻሉ ዝርያዎችን የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት 300 ሺህ ሄክታር ብቻ የነበረው የዞኑ የቡና ሽፋን አሁን ላይ ከ600 ሺህ ሄክታር በላይ መድረሱን ተናግረዋል።

በዘንድሮው ዓመትም 700 ሚሊዮን ችግኞችን ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለመትከል ታቅዶ ስራው ተጀምሯል ብለዋል።
የማና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሰመሩዲን አህመድ፤ በወረዳው 9 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና ለመሸፈን ታቅዶ በተጀመረው ስራ፣ በዛሬው ዕለት ብቻ በህዝብ ተሳትፎ በ100 ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ መተከሉን ገልጸዋል።

የወረዳው አርሶ አደሮች በክላስተር ተደራጅተው በመስኖ ማልማት ከጀመሩ ወዲህ ምርታማነታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንም አክለዋል።
የማና ወረዳ ዶዩ ቢቂላ ቀበሌ አርሶ አደሮች የሆኑት ጋሊ አባዝናብ እና ሀፊዝ በድሩ በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም ቡናን በግላቸው ለማምረት ባደረጉት ጥረት ያገኙት የነበረው ምርት አነስተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

"አሁን ላይ ግን በክላስተር ተደራጅተን ማምረት በመጀመራችን ተጠቃሚ መሆን ችለናል፤ ምርትና ምርታማነታችንም እያደገ መጥቷል" ብለዋል።
አርሶ አደሮቹ አክለውም፣ በአሁኑ ወቅት አስፈላጊው ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው በመሆኑ በዘንድሮው የምርት ዘመን ከፍተኛ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
ሀዋሳ፣ ነሐሴ20/2018 (ኢዜአ)፡-በሀዋሳ ከተማ የተጀመሩ የሐይቅ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ...
Aug 27, 2026
ሐረሪ ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል የኢንቨስትመንት ፍቃድ እና መሬት ወስደው ወደ ግንባታና ማምረት ባልገቡ 12 ባለሀብቶች ላይ የኢንቨስትመንት...
Aug 14, 2026
ደሴ፤ነሐሴ 6/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ173 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠ...
Aug 13, 2026
ባሕር ዳር ፤ ሐምሌ 23/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር...
Jul 31, 2026