🔇Unmute
ጅማ ፤ጳጉሜ 5/2018 (ኢዜአ)፡-ሜጋ ፕሮጀክቶችና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የነገዋን ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አቅም በጠንካራ መሠረት ላይ ለመገንባት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ምሁራን ገለጹ።
ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሀገሪቱን የልማት ምህዳር እና የከተሞች ገጽታ የሚቀይሩ በርካታ ግዙፍ የልማትና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በስፋት ስትተገብር ቆይታለች።
ከእነዚህም መካከል ሀገሪቱን የንጹህ ኤሌክትሪክ ኃይል ማዕከል የሚያደርጋት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የከተሞችን ጽዳት፣ ጤናማነትና የመሳብ አቅም ያሳደገው የኮሪደር ልማት፣ የወደፊት ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስን የሚያዘምኑ የኤርፖርትና የባቡር መስመር ማስፋፊያዎች፣ እንዲሁም በገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ ስር የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ይጠቀሳሉ።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን የመሠረተ ልማት እጥረት በመቅረፍ፣ ለሚሊዮኖች የሥራ ዕድል በመፍጠርና የኢንዱስትሪ ሽግግርን በማፋጠን ረገድ የጎላ ሚና እያበረከቱ ይገኛሉ።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንዳሉት፤ ሜጋ ፕሮጀክቶቹ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻል ባሻገር የክልላዊና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድጉ፣ ለስራ እድል ፈጠራና ለኢንዱስትሪ እድገት መንገድ የሚከፍቱ ስልታዊ የልማት እርምጃዎች ናቸው።
በዩኒቨርሲቲው የሕግ እና አስተዳደር መምህር ደሊል አህመድ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ የልማት ሥራዎች የኢትዮጵያን የወደፊት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አቅም ለመገንባት ጠንካራ መሠረት እየጣሉ ይገኛሉ።
በተለይም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር የኢትዮጵያውያን አንድነትና ብሔራዊ ኩራትን የሚያሳይ ምልክት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በከተሞች እየተካሄዱ የሚገኙት የኮሪደርና የመዝናኛ ስፍራዎች ልማት የቱሪዝም ዘርፉን ለማስፋፋት፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የከተሞችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን መምህር ደሊል አስረድተዋል።
መምህር ደሊል እንደገለጹት፣ የተጀመረው የልማት ጉዞ ዘላቂነት እንዲኖረው ሰላምን ማስከበርና የልማት እንቅስቃሴዎችን ማገዝ ያስፈልጋል።

በሌላ በኩል በዩኒቨርሲቲው የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምህር ጌታቸው ጥላሁን (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የኃይል ማመንጫ፣ የመንገድና የአየር ማረፊያ ግንባታዎችን ጨምሮ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ከተማን ከገጠር በማስተሳሰር የሕዝብን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው።
ጌታቸው(ዶ/ር) አክለውም፣ አሁን በተጣለው ጠንካራ መሠረት ላይ በመነሳት የነገዋን ኢትዮጵያ የመገንባቱ ሂደት በተማረና በብቁ የሰው ኃይል ላይ የሚመሠረት እንደሚሆን ገልጸዋል።
ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ያሉትን ማዕከላት ማጠናከር፣ ወጣቶችን በዕውቀት፣ በሙያ ብቃትና በሥነ-ምግባር ለማነጽ የሚደረገውን ጥረት የሚያፋጥንና ለሀገሪቱ የወደፊት ዕድገት ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ጠንካራና ተጠያቂነት ያላቸው ተቋማት መኖር የነገዋን ኢትዮጵያ ከመገንባት አኳያ ወሳኝ መሆኑን ጌታቸው (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በተለይም የዴሞክራሲ፣ የሕግና የሚዲያ ተቋማት ነፃና ጠንካራ ሆነው ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ ማድረግ፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበርና ሙስናን መዋጋት ለሀገሪቱ መረጋጋትና ለኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ አስረድተዋል።
ምሁራኑ አክለው እንዳመለከቱት፤ ኢትዮጵያ በልማት ሥራዎች፣ በሰው ኃይል ግንባታና ተቋማትን በማጠናከር ረገድ የምታደርገው ጉዞ የተሻለ ነገን ለመገንባት ተስፋ ሰጪ ናቸው።
ይህ ጉዞ ዘላቂ ውጤት እንዲያመጣ ግን ሰላምን፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን፣ የሰው ኃይል ልማትንና ጠንካራ ተቋማትን በተጓዳኝ ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሀዋሳ፣ ነሐሴ20/2018 (ኢዜአ)፡-በሀዋሳ ከተማ የተጀመሩ የሐይቅ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ...
Aug 27, 2026
ሐረሪ ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል የኢንቨስትመንት ፍቃድ እና መሬት ወስደው ወደ ግንባታና ማምረት ባልገቡ 12 ባለሀብቶች ላይ የኢንቨስትመንት...
Aug 14, 2026
ደሴ፤ነሐሴ 6/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ173 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠ...
Aug 13, 2026
ባሕር ዳር ፤ ሐምሌ 23/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር...
Jul 31, 2026