የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ልዩ ዘገባ

የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች በጓሮ አትክልት ልማት ሥራ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው

Nov 26, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

ወላይታ ሶዶ፤ ሕዳር 17/2018 (ኢዜአ)፦ በወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ ያገኙትን ስልጠና ተጠቅመው በአነስተኛ ቦታ ባከናወኑት የጓሮ አትክልት ልማት ሥራ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ነዋሪዎች ገለጹ።

የወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ በበኩሉ የጓሮ አትክልት ልማት ሥራው በከተማ ግብርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑን አስታውቋል።

የከተማ ግብርና አካል የሆነውና በቤተሰብ ደረጃ የሚከናወነው የጓሮ አትክልት ልማት ህብረተሰቡ የተለያዩ አትክልቶችን በጓሮው በቀላሉ አልምቶ ጤናውን ለመጠበቅ የሚያግዝ ነው።


አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት የወዳደቁ ቁሶችን በመጠቀም በአነስተኛ ቦታ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማትና ዶሮ በማርባት ተጠቃሚ እየሆኑ መጥተዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ተሻለ ዋቤሎ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በግቢያቸው ምንም አይነት የጓሮ አትክልት ሳያለሙ ለዓመታት ማሳለፋቸውን አስታውሰዋል።


በኮሌጁ በቤተሰብ ደረጃ በሚከናወን የጓሮ አትክልት ልማት ሥራ ባገኙት ስልጠና መሰረት ላለፉት ሦስት ዓመታት በወዳደቁ ዕቃዎች ላይ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ለቤት ፍጆታ ማዋላቸውን ገልጸዋል።

በአነስተኛ ቦታ በመደርደሪያና ግድግዳ ላይ በመስቀል ከሚያከናውኑት የጓሮ አትክልት ልማት ጎን ለጎን ዶሮ እያረቡና ተረፈ ምርቱን ለማዳበሪያነት እየተጠቀሙ መሆኑን ተናግረዋል።


የከተማው ነዋሪ አቶ አዳሙ ዲማ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም ለቤት ፍጆታ የሚውል ጎመን፣ ሽንኩርትና ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን ለመግዛት ከፍተኛ ወጪ ያወጡ እንደነበር ገልጸዋል።


ከአንድ ዓመት በፊት ከኮሌጁ ያገኙትን ስልጠና ተግባራዊ በማድረግ በመኖሪያ ቤታቸው ባለ አነስተኛ ስፍራ አትክልት አልምተው መጠቀም መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የጓሮ አትክልት ልማት ሥራቸው የቤተሰብን ወርሃዊ የአትክልት ፍጆታ በመሸፈን ከወጪ እንደታደጋቸው ተናግረዋል።


በወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ የአትክልትና ዕጽዋት ሳይንስ ባለሙያ መምህር ደበበ ደጉ፤ በቤተሰብ ደረጃ የሚከናወነው የተቀናጀ የጓሮ አትክልት ልማት ሥራ የከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


ባላቸው ጠባብ ቦታ የወዳደቁ ዕቃዎችን በመጠቀም የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን አልምተው እንዲጠቀሙ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

ኮሌጁ በወላይታ ሶዶና አርባ ምንጭ ከተሞች እንዲሁም በተለያዩ ዞኖች ለሚገኙ ከ1 ሺህ 500 በላይ ነዋሪዎች ስልጠና መስጠቱን ተናግረዋል።

ሥራው በአነስተኛ ቦታ፣ በግድግዳና መደርደሪያ ላይ ማንጠልጠያ በማዘጋጀት ጭምር የሚከናወን መሆኑን ጠቁመው፣ ልማቱ በከተማ ግብርና እና በሌማት ትሩፋት መርሀግብር በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።


በቤተሰብ ደረጃ የሚከናወነው የጓሮ አትክልት ልማት ሥራ ነዋሪዎች የተለያዩ አትክልቶችን በደጃቸው እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም ባለሙያው ተናግረዋል።

በኮሌጁ የምርምር ስርጸትና ህትመት ክፍል አስተባባሪ መምህር መስፍን ጌታቸው ፤ ኮሌጁ በተቀናጀ የጓሮ አትክልት ልማት ስራ ሞዴል ማሳ በማዘጋጀት የቴክኖሎጂና የክህሎት ሽግግር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


በቤተሰብ ደረጃ በሚከናወን የተቀናጀ የጓሮ አትክልት ልማት ሥራ የከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ውጤት ተገኝቶበታል ብለዋል።

ኮሌጁ ስልጠና ተከታትለው ለሚወጡ ዜጎች ዘር ከመስጠት ጀምሮ የባለሙያ ድጋፍና ክትትል በማድረግ እንደሚያግዝም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.