🔇Unmute
ሐረር፤ የካቲት 24/2018(ኢዜአ)፡- በለውጡ ዓመታት በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን፣ ጎዴ እና ደገሃቡር ከተሞች ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች መከናወናቸው ተገለጸ።
የሶማሌ ክልል ሰፊ የተፈጥሮ ሃብትና እምቅ የልማት አቅም ያለው ቢሆንም፣ ለበርካታ አስርት ዓመታት ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠውና ልማት ተነፍጎት ቆይቷል።
ሆኖም ባለፉት የለውጥ ዓመታት ክልሉን ወደተሟላ የልማት እንቅስቃሴ በማስገባት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።
በለውጡ ዓመታት የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ደግሞ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ከማድረግም ባለፈ ለሀገራዊ እድገትና ተጠቃሚነት የሚኖረው ድርሻ የላቀ መሆኑ ይታመናል።
ከዚህ አንፃር በክልሉ ሸበሌ ዞን፣ ጎዴ እና ደገሃቡር ከተሞች የተከናወኑና በሂደት ላይ ያሉ የልማት ሥራዎችን በማስመልከት ኢዜአ የሚመለከታቸውን የሥራ ሃላፊዎችና ነዋሪዎችን አነጋግሯል።
አስተያየት ሰጪዎቹም በለውጡ ዓመታት በጎዴ እና ደገሃቡር ከተሞች ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች መከናወናቸውንና በሂደት ያሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የሸበሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዲ ፋራህ፤ በዞኑ በገጠርና በከተሞች በተለይም የመንገድ መሰረተ ልማት በስፋት መከናወኑን ገልጸዋል።
ይህም የልማት ሥራን ከማፋጠን ባለፈ የግብርና ምርቶችን ለሀገር ውስጥና ለአጎራባች ሀገራት በቀላሉ ወደ ገበያ ለማቅረብ ማስቻሉን ተናግረዋል።
የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮን ጨምሮ ሌሎች የውሃ አቅርቦትን የሚያሻሽሉ ሥራዎች በዋቢ ሸበሌ ወንዝ ዳርቻዎች መከናወናቸው ለአርሶ አደሩ የግብርና ውጤታማነት አስተዋጾ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር በተያያዘም የተለያዩ ፋብሪካዎችን ሥራ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በበጀት ዓመቱ በዞኑ ለ24 ስዓት የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት ያገኙ ወረዳዎች እንዳሉ ገልጸው፣ የኔትወርክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋትም የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
በአካባቢው በልማት ለተመዘገበው አበረታች ውጤት ሰላም የጎላ አስተዋጾ ማድረጉን ጠቅሰው፣ የጸጥታ ሥራው ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በቅንጅት መከናወኑን አክለዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በጎዴ ከተማ በተከናወነው የሰላምና የልማት ሥራዎች ከተማዋ እድገት እየተፋጠነና ህዝቡም ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የጎዴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱላሂ አሊ ናቸው።

በከተማው ትልቅ የውሃ ፕሮጀክት መገንባቱን ጠቁመው በዚህም የከተማው ህዝብ ህይወት እየተቀየረ መጥቷል ብለዋል።
በከተማው 16 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ መገንባቱን ገልጸው ሌሎች አፈጻጸማቸው 80 በመቶ የደረሱ መንገዶችም በሚቀጥሉት ሦስት ወራት እንደሚጠናቀቁ አመልክተዋል።
እነዚህ የልማት ሥራዎች ከተማዋን ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ከማድረግ ባለፈ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም ከንቲባው አብዱላሂ አክለዋል።
የደገሃቡር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዲሀኪም መአሊን በበኩላቸው ከተማዋ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የሰላምና ልማት ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አንዷ ናት ብለዋል።
በዚህም በተለይ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢው የሰፈነው ሰላም ህዝብን ወደ ልማት በማስገባት ተጠቃሚ እንዲሆን ከማስቻሉ ባለፈ ከተማዋን ወደተሻለ እድገት እያሸጋጋራት መሆኑንም አመልከተዋል።
የጎዴና የቀብሪደሃር ከተሞች ነዋሪ የሆኑት ሀሰን ኡመር እና አብዱላሂ ኡመር በየበኩላቸው እንዳሉት በአካባቢው የሰፈነውን ሰላም ተከትሎ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።

በተለይ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተከናወኑ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የከተሞችን እድገት እያፋጠኑ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት አካላት ወደአካባቢው መምጣት ልማትን ለማፋጠን እያገዘ መሆኑን ገልጸው፣ በቅርቡ የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችም ለክልሉም ሆነ ለሀገር ጉልህ ፋይዳ ስላላቸው ለስኬታማነታቸው የበከሉቻውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025