🔇Unmute
አምቦ፤ ሰኔ 9/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሸዋ ዞን የተገነቡ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለረጅም ጊዜ ሲያነሱት የነበረውን የልማት ጥያቄ እንደመለሰላቸው የዞኑ ነዋሪዎች ገለጹ።
ምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍተኛ የግብርና ምርትና የንግድ እንቅስቃሴ ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ቀደም ሲል የነበሩት የመሰረተ ልማት እጥረቶች ምርትን በወቅቱና በጥራት ወደ ገበያ ለማቅረብ እንዲሁም ነዋሪዎች ፈጣን ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር አድርገው ቆይተዋል።
ይህንን ክፍተት ለመሙላት በፌደራል፣ በክልልና በዞኑ አስተዳደር የተቀናጀ ጥረት የተገነቡት የልማት ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸው በነዋሪዎች ህይወት ላይ አዎንታዊ ለውጥ በማምጣት ላይ ናቸው።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዞኑ ነዋሪዎች እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁት የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች፣ ቀደም ሲል የነበሩትን ክፍተቶች በከፍተኛ ደረጃ በመፍታት የቆየ ጥያቄያቸውን እየመለሰላቸው ነው።
ከነዋሪዎቹ መካከል የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ነዋሪ የሆነው ወጣት ዳንኤል ባይሳ፤ በወረዳው የተከናወኑ የንጹህ መጠጥ ውሃና የመንገድ ግንባታ ስራዎች የአካባቢውን ማህበረሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ናቸው።
በተለይም የመንገዱ መገንባት የሚያመርቱትን ምርት በቀላሉ ወደ ገበያ በማቅረብ ያጋጥም ለነበረው ችግር ዘላቂ መፍትሄ መስጠቱን ጠቁሟል።
ፕሮጀክቶቹ በተለይም ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል መፍጠራቸውን ጠቅሶ፤ እሱም የዚህ እድል ተጠቃሚ መሆኑን ተናግሯል።
የተገነቡ ልማቶችን ደህንነት በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም ተናግሯል።
ሌላኛዋ የአምቦ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ጋዲሴ ቡልቶ በበኩላቸው፤ ለብዙ ዓመታት በአካባቢያቸው የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ በኑሯቸው ላይ ከፍተኛ ችግር አድርሶባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ግን የመንገድ፣ የትምህርት ቤት እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ የመሰረተ ልማት ዝርጋታው የቆየ ጥያቄያቸውን የመለሰና በተለይም ሴቶችን እኩል ተጠቃሚ ያደረገ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አበበ ጨመዳ፤ በዞኑ በበጀት ዓመቱ ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ሲከናወን መቆየቱን ገልጸዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል የመንገድ፣ የትምህርት፣ የጤና እና የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መንግስት በበጀት ዓመቱ የህዝብ ጥያቄ የነበሩ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ፣ በጥራትና በብዛት አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እያደረገ መሆኑንም አክለዋል።
በዞኑ በ2018 በጀት ዓመት የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ 675 የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመስራት ታቅዶ፣ እስካሁን 519 የሚሆኑት ተገንብተዋል ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቁ የዞኑ ህብረተሰብ ያበረከተው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን የገለጹት ምክትል አስተዳዳሪው፤ ለአብነትም የባህላዊ ፍርድ ቤቶች፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ እና ሌሎች የልማት ስራዎች እንዲስፋፉ ህዝቡ ትልቅ እገዛ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በበጀት ዓመቱ የታቀዱ የልማት ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ የዞኑን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ መሆኑንና ለበርካታ ስራ አጥ ወጣቶችም የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።
እነዚህ በህዝብና በመንግስት ተሳትፎ የተገነቡ ፕሮጀክቶች በሁለት ዙር ተከፍለው የምርቃ መርሃ ግብር እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው፤ በመጀመሪያው ዙር 391 ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል ብለዋል።
በሁለተኛው ዙር ደግሞ ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ 128 ፕሮጀክቶች በቅርቡ የምርቃ መርሃ ግብር እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ባህር ዳር፤ ሰኔ 2/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ዘርፉ በጥናትና ምርምር በመታገዙ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እየፈጠረና ከፍተኛ የገቢ...
Jun 10, 2026
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2018 (ኢዜአ)፦ ህዝባችን ለአገልግሎት ፍለጋ ጊዜና ገንዘቡን ሳያባክን ሃብቱን ለልማት እንዲያውል የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥ...
Jun 9, 2026
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2018 (ኢዜአ)፦ የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ መመረቅ ፍትሐዊና ሚዛናዊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታን የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቅላ...
May 28, 2026
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡- ቱሪዝም የኢኮኖሚያችን አንዱ ምሰሶ እንደመሆኑ የሀገራዊ ዕድገታችንን የወደፊት አቅጣጫ እየቀረጸ ያለ ዘርፍ መሆኑ...
Apr 20, 2026