🔇Unmute
ሮቤ፣ ሰኔ 24/2018 (ኢዜአ)፡- የኦሮሚያ ክልል የአርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ ኑሮ ለማሻሻልና የእንስሳት ሀብቱን ከአደጋ ለመጠበቅ ተግባራዊ ያደረገው የእንሰሳት ኢንሹራንስ ውጤት እያመጣ መሆኑን የክልሉ መስኖና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ገለጸ።
የእንስሳት ኢንሹራንሱ የአርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ የአደጋ ስጋት ተጋላጭነት ለመቀነስና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተመልክቷል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊና የአርብቶ አደር ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሮባ ቱርቼ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት፣ በክልሉ የአርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል።
በተለይ አርብቶ አደሩ የድርቅ ተጋላጭነቱን እንዲቀንስና ከእንስሳት ሀብቱ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያግዙ አሠራሮች መዘርጋታቸውን አመልክተዋል።
ከዚህ ውስጥ የእንስሳት ኢንሹራንስ ፖሊሲ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢንሹራንሱ የአርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ የድርቅ ተጋላጭነት ለመቀነስ እና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እያገዘ መምጣቱን ተናግረዋል።
የአደጋ ስጋት ቅነሳ ፕሮጀክቱ በክልሉ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱንም ገልጸዋል።
በእንስሳት ኢንሹራንሱም መኖ፣ ውሃና መድኃኒት እንደሚገዛ የጠቀሱት ኃላፊው፤ ድርቅ ሲያጋጥም ደግሞ እንስሳቱ ሳይጎዱ ወደ ጥሬ ገንዘብ የሚለወጡበት አሠራር ጭምር የሚተገበርበት መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም በበጀት ዓመቱ ከ22 ሺህ ለሚበልጡ የኢንሹራንስ አባል አርብቶ አደሮች ከ413 ሚሊዮን ብር በላይ ለመኖ እና ውሃ አቅርቦት እንዲሁም ለእንስሳት ጤና መጠበቂያ የሚሆን ክፍያ መፈጸሙን ገልጸዋል።
በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት አነስተኛ የዝናብ እጥረት በተከሰተባቸው የአርብቶ አደር አካባቢዎች የጎላ ችግር ሳያጋጥም፣ በተፈጠረው አካባቢያዊ አቅም ድርቁን መቋቋም መቻሉ የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ከኢንሹራንሱ ጎን ለጎን የሚስተዋለውን የእንስሳት መኖ እጥረት ለመቅረፍ፣ በተለያዩ ዞኖች ለግጦሽ ከተለዩ ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ከ409 ሺህ 900 ቶን በላይ የመኖ ሳር በማምረት ማከማቸት መቻሉን ገልጸዋል።

የእንስሳት መኖን ለማከማቸት የሚያግዙ ከ17 የሚበልጡ ትላልቅ የማከማቻ ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውንም አክለዋል።
የአርብቶ አደሩን የእንስሳት ገበያ በየአካባቢው ተደራሽ በማድረግና የግብይት ሰንሰለቱን ለማሳለጥ የተገነቡት 20 የሚሆኑ ማዕከላት፣ አርብቶ አደሩ ከገዢው ጋር በቀጥታ ተገናኝቶ እንዲገበያይ እያደረጉ መሆኑን አቶ ሮባ አስታውሰዋል።

የክልሉ መንግሥት ይህንን የእንስሳት ኢንሹራንስ ይበልጥ ተደራሽ በማድረግ፣ የአርብቶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ ለማዘመንና አካባቢያዊ ተጽዕኖዎችን የመቋቋም አቅምን ለመገንባት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።
ኮምቦልቻ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፡- የአዋሽ-ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ ባቡር መስመር ፕሮጀክት ጥገናን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ...
Jul 1, 2026
አዲስ አበባ፤ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ጣሊያን የ70 ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱ በረጅም ጊዜ የሚከፈል የብድር ስምምነ...
Jun 30, 2026
ባሕር ዳር፤ ሰኔ 19/2018(ኢዜአ)፡- በተቋማት እየተካሄደ የሚገኘውን የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም በላቀ የአመራር ጥበብ በመፈፀም የመልካም አስ...
Jun 27, 2026
አሶሳ፤ሰኔ 16/2018 (ኢዜአ)፦ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ከተረጂነት ለመላቀቅ የተያዘውን ዕቅድ የሚያሳኩ ናቸው ሲሉ የቤ...
Jun 24, 2026