🔇Unmute
ዲላ፣ ጥቅምት 29/2019 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የእንሰት ተክልን ከተለመደው የአርሶ አደር ጓሮ እርሻ ወደሰፊ ማሳ በማሸጋገር የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት አስታወቀ።
በክልሉ ለእንሰት ተከል በተሰጠው ልዩ ትኩረት ዓመታዊ የምርት መጠንን ማሳደግ መቻሉም ተመላክቷል።
እንሰት በደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍል የምግብ ምንጭ ብቻ ሳይሆን የህዝቡ ባህልና የአኗኗር ስርዓት ጭምር ነው።
ተክሉ ለአፈር ለምነት መሻሻል፣ ምርቱ ሲደርስ ደግሞ የምግብ ምንጭ አልፎም ተረፈ ምርቱ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ በመሆኑ በክልሉ አርሶ አደሮች ዘንድ ተመራጭና ተፈላጊ ነው።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት ዳይሬክተር አብዮት መብራቴ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እንሰት እርጥበት በመያዝና በማስረግ ድርቅን የመቋቋም ከፍተኛ አቅም አለው።
በተለይ ዓመቱን ሙሉ ወቅት ሳይመርጥ ምርት የሚሰጥ ሰብል መሆኑ ለምግብ ዋስትና ችግር ፍቱን የሆነ ሀገራዊ መፍትሄ ነው ብለዋል።
ይሁንና ቀደም ሲል በቂ ትኩረት አለማግኘቱ የምግብ ዋስትና ችግርን የማቃለል አቅሙን በአግባቡ እንዳንጠቀም እንቅፍት ሆኗል ነው ያሉት።
ኢኒስቲትዩቱም የምርት ዝግጅቱን ለማዘመንና በሽታን የመቋቋም አቅሙን ለማሳደግ ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን በቅንጅት ማከናወኑን ተናግረዋል።

በዚህም ተቋሙ 700 የእንሰት ዝርያዎችን ከማቆየቱ ባለፈ በሽታን መቋቋም የሚችሉ፣ በአጭር ጊዜ ወስጥ ምርት የሚሰጡና ድርቅን የመቋቋም ከፍተኛ አቅም ያላቸውን 7 ዝርያዎችን የማላመድና የማስፋት ሥራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
"እንሰት በተናጠልም ሆነ በስብጥር የሚለማ ለግብርና ምርት ምቹ የሆነ ሰብል ነው" ያሉት አብዮት (ዶ/ር)፣ በተለይ እርጥበትን በመያዝና በማስረግ ለቡናና ስራስር ሰብሎች ልማት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
እንሰት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በተለይ በእርሻ ደረጃ በጌዴኦ ዞን በስፋት እንደሚለማ ገልጸው፣ በክልሉ የእንሰት ተክልን ከአርሶ አደር ጓሮ ወደ እርሻ ማሳ በማስፋት የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንሰት ምግብ ብቻ ሳይሆን የዞኑ ህዝብ ባህልና የአኗኗር ስርዓት ጭምር ነው ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ በድሉ አየለ ናቸው።
በዞኑ ከ46 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በእንሰት ልማት የተሸፈነ ሲሆን፣ ምርታማነትን ለማሻሻል በተደረገ ርብርብም ዓመታዊ የምርት መጠኑን 3 ሚሊዮን 100 ሺህ ኩንታል ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

እንሰት ከምግብ ዋስትና ባለፈ ተረፈ ምርቱ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑን ጠቅሰው በሩብ ዓመቱ ብቻ ከ22 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ቃጫ ለገበያ ቀርቧል ብለዋል።
በዚህም ገመድን ጨምሮ ለተለያዩ የእደ ጥበብ ውጤቶችና ለግንባታ ግብዓትነት በማዋል ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት ምርቱን የሚያቀነባብር ኢንዱስትሪ ለመክፈት የጥናት ሥራ መጠናቀቁንም አመልክተዋል።

በዞኑ ወናጎ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ውዴ ጥላሁን በበኩላቸው፤ እንሰት ምግባቸውም መተዳደሪያቸውም መሆኑን ተናግረዋል።
እንሰት ከደረሰ በቁሙ ይሸጣል ቆጮ ሆኖም ለምግብነት ይውላል ያሉት አርሶ አደሯ፣ በዘመናዊ መንገድ በማምረት ለምርት የሚደርስበትን ጊዜ ወደ ሁለት ዓመት ዝቅ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
እንሰት የአፈር ለምነት ከማሻሻል ባለፈ ተረፈ ምርቱ ገቢ እያስገኘላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ከተክሉ የሚገኘውን ቃጫ በኪሎ 80 ብር በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ጎንደር ፣ ጥቅምት 29/2019 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ቀድመው የደረሱ ሰብሎችን በቴክኖሎጂ ታግዞ የመሰብሰብ ሥራ በተፋጠነ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ በም...
Nov 9, 2026
ዲላ፣ ጥቅምት 25/2019 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር መንገድ ተደራሽነትን በማሳደግ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራት እ...
Nov 5, 2026
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2019 (ኢዜአ)፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኃይል ሴክተር ሪፎርም ኢንቨስትመንትና ማዘመኛ ምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚው...
Oct 14, 2026
መቱ፤ መስከረም 12/2019 (ኢዜአ):- በኢሉባቦር ዞን ከቡና ምርት የሚገኘውን ገቢና የአካባቢውን አምራቾች ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ በቡና ጥራት አጠባበቅና...
Sep 23, 2026