
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2017(ኢዜአ)፦ ነዳጅን ጨምሮ ስትራቴጂክ የሚባሉ ሸቀጦች አስተማማኝ አቅርቦት እንዲኖራቸው መንግስት ከፍተኛ ድጎማ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
መንግስት ባለፉት ዓመታት ከ267 ቢሊዮን ብር ለነዳጅ ድጎማ ማድረጉንም ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ በዘንድሮው በጀት ዓመት ብቻ ለነዳጅ ድጎማ ተጨማሪ 100 ቢሊዮን ብር በጀት መጽደቁን አውስተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ የነዳጅ አቅርቦት እና ድጎማን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተጠናክሮ ለኢኮኖሚው ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ሰፊ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ማሻሻያው የውጪ ምንዛሪ ግኝቱ በከፍተኛ ደረጃ እንዲሻሻ፣ ከልማት አጋሮች ጋር ያለው የልማት ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የኤክስፖርት አፈጻጸም እንዲሻሻል ጨምሮ የባንኮች የቁጠባ መጠን እንዲያድግ ብሎም በሁሉም መስኮች ውጤታማ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
የምንዛሬ ተመኑ በገበያ እንዲወሰን ከመደረጉም ሊመጡ የሚችሉ የዋጋ ጭማሪዎች ህብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳያሳድሩም ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።
በዚህም ነዳጅን ጨምሮ ስትራቴጂክ የሚባሉ ሸቀጦች አስተማማኝ አቅርቦት እንዲኖራቸው መንግስት ከፍተኛ ድጎማን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ለአብነትም ለአፈር ማዳበሪያ፣ ለነዳጅ፣ ለደመወዝ ጭማሪ፣ ለመድኃኒት፣ ለመሠረታዊ ሸቀጦች፣ ለከተማና እና ገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ጨምሮ ለሌሎችም በዓመት ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በሕብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳያስከትልም ሪፎርሙ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ኃላፊነት እየተሰራ ስለመሆኑ ነው ያነሱት።
መንግስት በሀገሪቷ አስተማማኝ የነዳጅ አቅርቦት እንዲኖር በዓመት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በመመደብ ነዳጅን በማቅረብ ላይ እንደሚገኝም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በውጪ ምንዛሪ የሚገዛውን የነዳጅ ምርትም በሀገር ውስጥ በብር እንዲሸጥ ከማድረግ በተጨማሪ በከፍተኛ የመንግስት ድጎማ ወደ ህብረተሰቡ እንዲተላላፍ በመደረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት መንግስት በአጠቃላይ 267 ቢሊዮን ብር ለነዳጅ ድጎማ ማድረጉን ጠቅሰው በዓለም ዋጋ የሚገዛውን የነዳጅ ምርት ከዓለም ዋጋ በታች እንዲሁም ከጎሮቤት ሀገራትም ዋጋ በታች በከፍተኛ ድጎማ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
እያንዳንዱ ተጠቃሚ በሚገዛው ነዳጅ ላይ የመንግስት ድጎማ መኖሩን ያነሱት ሚኒስትሩ በዘንድሮው በጀት ዓመት ብቻ ለነዳጅ ድጎማ ተጨማሪ 100 ቢሊዮን ብር በጀት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ መደረጉንም አስታውሰዋል።
መንግስት በሀገሪቱ አስተማማኝ የነዳጅ አቅርቦት እንዲኖር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት።
በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ከውጪ የሚገባውን እንዲሁም በከፍተኛ ድጎማ ለህዝብ የሚቀርበውን የነዳጅ ምርት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በመንግስት ከፍተኛ ድጎማ የሚቀርበውን የነዳጅ ምርት በኮትሮባንድ ወደ ጎሮቤት አገራት እንዳይወጣ ግብረ ሃይል ተቋቆሞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የነዳጅ የግብይት ስርዓቱን የማዘመን ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል
አዳማ፤ጳጉሜን1/2018(ኢዜአ)-መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ በፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ለመከላከል ትኩረት መሰጠቱን የኦሮ...
Sep 7, 2026
ጅማ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ):- ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ ወደ መስኖ ልማትና ሜካናይዜሽን እየተደረገ ያለው ሽግግር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ውስጥ አዲስ ምዕራፍ...
Sep 3, 2026
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 21/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የጥጥ ልማትን በጥራትና በብዛት በማምረት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች በግብአትነት ለማቅረብ ልዩ ትኩረት ...
Aug 28, 2026
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር በምርምር፣ በሰው ሃይል ልማት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር...
Aug 21, 2026